Monday, July 09, 2018

ረቢ

ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ!
መምህር ሆይ
ይህን ሁሉ ዘመን ደብተር ተሸክሜ፣
ዘመኔን ቆንጥሬ እድሜየን ዘግኜ፣
ቀኔን አባክኜ ከፊትህ ታድሜ፣
ሌጣ አዕምሮዬን ለፍርጃ ሰጥቸህ፣
በገማ ቴዎረም በበሰበሰ ቃል ሞልተኸኝ ሰለቸህ።
በዚህ ሁሉ ዘመን
እድሌ ተስፋዬ ባንተ መዳፍ ወድቃ፣
አንተን በማዳመጥ ነፍሴ ማቃ ማቃ፣
የዛሬ እልፍ ዓመት በወጣ መረጃ፣
እውቀቴ ብቃቴ ባንተ ተፈርጃ፣
ይህን ሁሉ ዘመን
አንተ እኔን ብቻ ስትፈትን ስትለካ ፣ስትፈትን ስትለካ፣
የመንገዴ አቅኚ የጨለማዬ ጦር እያልኩህ ስመካ፣
ውሉ ሲመረመር የሆንህበት ምስጢር የህይወቴ ሳንካ፣
ወድቀሃል ያልኸኝ ለት፣ ሚዛንህ ሚዛኔ ሰባራ ነው ለካ።
ቀድሞስ አንስታይን መች ባንተ ተለካ!
ራስህን ስፈር፣ ራስህን መርምር፣ ራስህን ለካ።
ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ!
እኔን ብሎ ሰሚ አንተን ብሎ ብርሃን ድንቄም መምህር እቴ!
ይህን ሁሉ ዘመን እድሜዬን ቀንጥሼ እኔን በመስጠቴ፣
ደንቆሮ ስትለኝ አንተን አይጨምርም እስኪ እንደው በሞቴ?
ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ!
እነ ዛራ’ስቱራ፣ እነ ክሪሽና
ሶቅራጥስ፣ፕሉቶ፣ እየሱስ ክርስቶስ ባለፉበት መንገድ፣
የምትንገዳገድ የምትወላገድ፣
ትውልድ የምትገድል በቅምጥ “ጀኖሳይድ”
ሆላ መምህር ሆላ፣ሆላ ረቢ ሆላ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ።
ይህን ሁሉ ዘመን አድምጨህ አድምጨህ
ተስፋየ ካጨጨ ካጣሁ አንድም መላ፣
ወድቀሀል ብለሀል መቼስ አታስፈጨኝ ከእንግዲህ በኋላ።
ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ።
አርባ ‘ምስት ደቂቃ አርባ ‘ምስት ደቂቃ፣
እየተሰፈረች እድሜዬ ተሰረቃ፣
አስተምረኝ ብዬ ራሴን ሰጥቸው ነዝንዞኝ ሲያበቃ፣
ደግሞ ሌላ ነዝናዥ ጠመኔውን ይዞ ሲያስረኝ በፈረቃ፣
እንዲህ እንዲህ ተብላ ዘመኔ ተፍቃ፣
ሰሌዳ ሆኛለሁ ከእንቅልፌ ስነቃ።
ራሴን አገኘሁ ሆኘ ሰባራ እቃ።
መምህር እሽሩሩ፣
መምህር እሽሩሩ፣
ውረድ ከጀርባዬ እንግዲህ ይበቃል፣
ራሱን አስተምሮ አንስታይን ይነቃል።
ምንጭ፦ የቀንድ አውጣ ኑሮ በይስማዕከ ወርቁ

No comments:

Post a Comment