Tuesday, August 23, 2016

ሐርሞኒ

"ሐርሞኒ" የሚለው ቃል ጥሬ ትርጉሙ "ለተሻለ ውጤት ተጣጥሞ መገኘት" የሚል ይሆናል።ሐርሞኒ የነገሮች ሞገዳዊ ንዝረት (vibration)ተጣጥሞ የመፍሰስን ወይም ደግሞ የመጓዝን ዘይቤ የሚያመለክት ፊዚክሳዊ የተፈጥሮ ህግ ነው።አንድ ሙዚቀኛ አሪፍ ቃና ያለው ዘፈን ለማስማት የድምፅ አወጣጡን ከመሳሪያው ቅንብር ጋር ማስማማት ይጠበቅበታል። እንዲሁም አንድ ዳንሰኛ ከሙዚቃው ጋር በህብረት ካልደነሰ በስተቀረ ሳቢነት አይኖረውም። ሐርሞኒ ማለት እንግዲህ መጣጣም፣ቅኝት፣ግጥም፣መስማማት የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል። ሁሉም ነገር ከኢነርጂ የተሰራ እንደመሆኑ መጠን የሚወክልበት ንዝረታዊ ሞገድ አለው።

የሐርሞኒ ጉዳይ የሞገድ ጉዳይ ነው። ሁለት የተለያዩ ሞገዶች ተመሳሳይ የአቅጣጫና የንዝረት ሞገድ ባላቸው ቁጥር የበለጠ ተጣጥመው ይፈሳሉ። ይህ መሰሉ የሞገዶች መጣጣም (in phase)በመባል ይጠራል። እንዲሁም ሞገዶቹ የተለያየ የአቅጣጫ ፍሰት ካላቸው (out of phase)በመባል ይጠራሉ።ሞገዶቹ በመጀመሪያው የሞገድ ጥምረት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ እርስ በርስ የመደመር እና የመድመቅ ባህርይ ያላቸው ሲሆን በአንፃሩ ደግሞ በተቃራኒ አቅጣጫ በሚሆኑበት ጊዜ እርስ በእርስ የመጠፋፋት ባህርይን ይላበሳሉ።ለምሳሌ አንድን የሬድዮ ጣቢያ ድምፅ "ጃም" በማድረግ ድምፁ እንዳይሰማ ልናደርገው የምንችለው ድምፁ ከሚተላለፍበት የድምይዝ ሞገድ በተቃራኒ የሚፈስ ሞገድ በመልቀቅ ነው ።የትኛውም ነገር በሞገድ የሚገለፅ ነው ።ምናልባት የሞገዱ መጠን ሊያንስ ወይም ሊበዛ ግን ይችላል።ሐርሞኒም ይህን መሰል የተፈጥሮ ህግ የሚያንፀባርቅ ህግ ነው።

በዚህ ህግ መሰረት የምንኖር ከሆነ (ህዝብና መንግስት እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ አፍ ተናጋሪ ሆነው መስራት ከቻሉ ለህዝብ ጥያቄ ቀጠተኛ መልስ የሚሰጥ መንግስት፣ መንስት ለሚያወጣቸው ህጎች የሚገዛ ህዝብ ካለ ፣የተጻፈውና ተግባር ላይ የሚውለው ህግ ተመሳሳይ ከሆኑ) ህይወታችን በጥሩ መንፈስና በሰላም የመምራት አቅም ይፈጠርልናል።በአንፃሩ ደግሞ ከዚህ ህግ በተቃራኒ ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ(መንግስት የህዝብን ጥያቄ ገልብጦ ከሰማ፣መንግስት ለሚያወጣቸው ህጎች ህዝቡ አልገዛም ካለ፣  የተፃፈው ህገ መንግስትና ተግባር ላይ የሚውለው ህግ ተቃራኒ ከሆኑ፣ የሰላም ጥያቄ ላነሳ ህዝብ የጦር ሰራዊት ከተመደበ ፣የምግብ እርዳታ ለሚፈልግ ማህበረሰብ መትረዬስ መላክ ከተጀመረ) የተለያዩ ግጭቶችንና ውጣውርዶችን እያስተናገድን መጓዝ ግድ ይሆንብናል።

ተፍጥሮ ህጎችና ፍላጎቶች አሏት።ከእነዚህ ህጎች ጋር ተጣጥሞ ለመስራት መሞከር  ቀጣይነት ላለው ህልውና ያበቃል።ተጣጥሞ ያለመስራት ደግሞ በተቃራኒው ያለመስማማትን ይፈጥራል ።ለምሳሌ የተፈጥሮን የሐርሞኒ ህግ  አለማክበርና በራስ ፍላጎት ብቻ የሚመራ አሰራር እንደ (global warming)አይነት ችግሮችን ያስከትላል።የመንግስት ህጎችና ፖሊሲዎች ጋር ነገሮችን አጣጥሞ ለመስራትና ለመኖር በቻልን ቁጥር የተረጋጋና ሰላማዊ ኑሮ መምራት ስንችል ከህግና ፖሊስ ጋር እየተጋጨን የምንሰራና የምንኖር ከሆነ ደግሞ ወደ ህግ ተጠያቂነትና ተቀጭነት ማምራታችን አይቀርም።እያንዳንዱ ማህበረሰባዊ ባህል የራሱ የሆነ ህግና ደንብ አለው።በዚህ መሰል ማህበረሰብ ውስጥ ለመኖር ከተፈለገ ህጉን ባናምንበት እንኳን በተቻለ መጠን ተቻችሎና አቻችሎ ለመኖር መሞከር መቻል አለብን።አለባብሳችን ድርጊታችን ነገራችን ባህርያችን ሙሉ በሙሉ አልያም ደግሞ በተወሰነ መልኩ የተጣጣመ መሆን አለበት።አለበለዚያ ግን ውግዘት ውስጥ እንገባለን።

ሐርሞኒ ሌላም ነገር አለው።የህሊና ህግ ።ሁላችንም ህሊና ያለን በመሆናችን በአእምሯችን ውስጥ የምንመራበት የሞራል ወይም የህሊና ህግ አለን።የዚህ ህግ መመሪያ በዙሪያህ ላሉት ነገሮች ሁሉ የተሻለና ጠቃሚ ነገር የማድረግ፣የማክበርና የመንከባከብ እንዲሁም ጥቅማቸውንና ተጠቃሚነታቸውን  የማስከበር ህግ ነው ።ይሁን እንጅ ጥቂት የማንባል ሰዎች ከዚህ መሰል ወርቃማ የአዕምሮ ህግ  ጋር የተጣጣመ ድርጊትና ንግግር ወይም አስተሳስብ የሌለን በመሆናችን በየጊዜው ከራሳችን ህሊና ጋር እየተጋጨን የውስጥ ኃይላችን እንዲባክን እንፈርድበታለን።ሰላምና ደስታ እናጣለን፤እንዲሁም የስራ ትጋታችን ይወርድብናል። ምክንያቱም በአዕምሯችን ውስጥ የተፈጠረው የሞገድ ግጭት ለኃይል ብክነት የዳረገን በመሆኑ ነው ።የፈጣሪ ህግም ጋር መጣጣም አለመቻል እንዲሁ ተመሳሳይ ውጤት ያለው ነው።

ሌላው በሁለት ሰዎች መካከል ያለ ስምምነታዊና ጥምረታዊ አኗኗርና አሰራር የሚኖረው ተፅዕኖ ነው። እርስ በእርስ የሚናበብና የሚግባባ የቡድን አባል ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው ።ሁለት ባልና ሚስትም በ"in phase"መርህ መጣጣም መግባባትና መናበብ ከቻሉ ኑሯቸው ሰላማዊ ፣ፍቅራዊና ስኬታማ የመሆን እድሉ የላቀ እንደሆነ ሁሉ በአንፃሩ ደግሞ የማይግባቡና የማይስማሙ ከሆነ እየኖሩ ያሉት "out of phase" በተባለው የሐርሞኒ ህግ ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ እርስ በእርስ መጠፋፋት(jamming effect)እንዲኖር ያደርጋል። የኑሮ መንፈሳቸውና ተስፋቸው ይበረዛል፤ሰላማቸውና ደስታቸው ይረበሻል፤የስራ ተነሳሽነት ኃይላቸው ይቀንሳል።ጤናማነታቸውና  ምርታማነታቸው እንዲሁ አብሮ ይወርዳል።ሁለት ባልና ሚስቶች ወይም ሁለት የንግድ ሽርኮች ተጣጥመውና ተግባብተው ውጤታማነታቸው በየግላቸው ከሚኖረው ድምር ውጤት በላይ የላቀ ይሆናል።በሐርሞኒ ህግ ሁለት በ"in phase"ውስጥ ያሉ ሞገዶች ሲደመሩ የሞገድ መጠናቸው (wave length)ከሁለቱ የድምር መጠን በላይ ነው ።ለምሳሌ"1+1=2" እንደሚባለው ሳይሆን ተጣጥመው የሚኖሩ ባልና ሚስት የሰላም፣የደስታ፣የጤናማነትና የስኬት ውጤታማነታቸው "1+1=3 ወይም 4" ይሆናል።ነገር ግን የእርስ በእርስ መጣጣምና  መግባባት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ውጤቱ 1+1=0ወይም-3" ሊሆን ይችላል።

ሁለት የተለያዩ ሰዎች በአንድ ነገር ላይ የተለያየ አቋም በመያዛቸው የተነሳ ብዙ ጊዜ በመካከላቸው ግጭት ይፈጠራል።ይሁን እንጂ ግጭቱ የተፈጠረው ሰዎቹ በነገሩ ላይ ያላቸውን አመለካከትና ፍላጎት ከሐርሞኒ ህግ ጋር ማጣጣም ባለመቻላቸው ነው ።ሁለት ሰዎች በአንድ ነገር ላይ የማይስማሙትና የሚጋጩት ሁለቱም የራሳቸውን ተጠቃሚነትና ተቀባይነት ብቻ ለማሟላት በመፈለጋቸው የተነሳ ነው።ይሁን እንጅ ሁሉም ሰው የራሱን ተቀባይነት ለማስፋት ፍላጎት እንዳለው መረዳት አለብን ።በሐርሞኒ ነገሮችን አጣጥመን የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የማንሰራና በዚህም መሰረት የማንስማማ ከሆነ ሊፈጠር የሚችለው ቀጣይ ጉዳይ ግጭት ነው።ይህ ደግሞ ለማንም አትራፊ አይደለም።

እንዲሁም አንድ ነገር እንዲኖረን እንፈልግ ይሆናል ።ለምሳሌ በዛ ያለ ገንዘብ።ገንዘቡን የማምጣት አካሄድ አለ፤እንዲሁም የመጣውን ገንዘብ አክብሮ በትክክል የመያዝና የማባዛት ሞገድ አለ።ሁለቱም ሞገዶች ከአስተሳስብና ከድርጊት መገዶች ጋር የሚጣመሩ ናቸው ።አንዱ በገንዘብ አቅሙ ትልቅ ደረጃ መድረስን ይፈልጋል፤ይሁን እንጅ ለዚያ ነገር የሚስፈልገውን አስተሳሰብ ፣አነጋገግርና ድርጊት ግን ተግባራዊ ሲያደርግ  አይስተዋልም።ወይም ገንዘብ ይፈልጋል ስለገንዘብ መጥፎነት ግን ይሰብካል።ወይም ደግሞ ብዙ ገንዘብ ይፈልጋል ብዙ ገንዘብ ማግኘት እንደሚቻል ግን አያምንም።ይህ መሰል በፍላጎትና በስሜት መካከል  ያልተጣጣመ የገንዘብ ሞገድ ዳር ሊያደርስ አይችልም ።የምንፈልገውን የትኛውንም ነገር ለማሳካት ከተፈለገው ነገር ጋር የተጣጣመ አስተሳሰብ እምነት፣ንግግር ድርጊትና ዝግጅት ያስፈልገናል።የዚያኛውን ሞገድ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚችል ሞገድ ማንገብ ያስፈልጋል።

በሐርሞኒ ህግ መሰረት ተጣጥመው መስራት ያልቻሉ ህዝብና መንግስት ፣ንግግሩና ግብሩ የሚቃረኑበት የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መሪ መጨረሻቸው ጥፋት ነው።በየሚዲያውና በየስብሰባው ስለ ዘላቂ ሰላም፣ስለ አረንጓዴ ልማት፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገሮች ተራ ስለመሰለፍ፣ እራስን በራስ ስለማስተዳደር፣ስለመሰብሰብ፣ ስለ መደራጀት ስለመናገርና ሃሳብን በነፃ ስለመግለፅ እና ስለ ሌሎችም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚስብክ፤  ተግባሩ ግን ህፃናትን አሳዳጊ አረጋውያንን ጧሪ ማሳጣት የሆነበት፣መላ ሀገሪቱን የደም አውድማ የሚያደርግ።  የማንነት ጥያቄ የሚያነሱትንና ሰላማዊ ሰልፍ የሚወጡትን "የእነ እንተና ተላላኪዎች" የሚል ስም በመስጠት በአስለቃሽ ጭስ እያፈነ በጥይት ድባቅ የሚመታ፣ጋዜጠኞችንና የፖሊቲካ ሰዎችን ሰብስቦ በጨለማ ቤት የሚያስር 10.ሚሊዬን ህዝብ በረሃበ እያለቀ ምናምንኛ ዓመቱን ለማክበር "ድል"ያለ ድግስ የሚደግስ፣ግስት  መጨረሻው ጥፋት ነው።

 "ተመሳሳይ ክንፍ ያላቸው ወፎች አንድ ላይ ይበራሉ ፤ባልና ሚስት ከአንድ ባህር ይቀዳል፤ጓደኛህን ንገረኝና አንተነትህን እነግርሃለሁ፤ሰው አካባቢውን ይመስላል የሚሉ አባባሎች የሚያንጸባርቁትም ምን ያህል በኑሯችን ውስጥ ከሰዎችም ሆነ ከአካባቢያችን ጋር ተጣጥመን ለመሄድ ያለንን ውስጣዊ ፍላጎትና ባህርይ ነው ።ይህም የሚያሳየው የሐርሞኒ ህግ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚሰራ መሆኑ ነው ።

ይህ ጽሑፍ አልፋና ኦሜጋ ከተሰኘው የዶ/ር አቡሽ አያሌው መጽሐፍ የተወሰደ ሲሆን ተንጋደው በቀይ ቀለም የተጻፉት  እራሴ የጨመርኋቸው ሀሳቦች ናቸው።

No comments:

Post a Comment