Monday, August 08, 2016

ፍልሰታ

 ፍልሰታ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማዛወር የነበሩበትን ሀገር ለቆ ወደ ሌላ ሀገር መሰደድ መፍለስ ማለት ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ሲባልም የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኒ ወደ ገነት መፍለስን በኋላም በገነት በእፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሣቱን ለማመልከት የሚነገር ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም 64 ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ በሞት ከተለየች በኋላ እንደ አንድ ልጅዋ ሞታ መነሣቷንና እርገቷን ያዩ ዘንድ ሐዋርያት ከነሐሴ 1 እስከ 16 የጾሙት ጾም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ከሰባቱ አበይት አጽዋማት አንዱ ሆኖ በቀኖና እንዲጾም ከተወሰነበት ጊዜ ጀምሮ ምእመናን ይጾሙታል፡፡

እመቤታችን በ5485 ዓ.ዓ ከአባቷ ከኢያቄም ከእናቷ ከሐና “እም ሊባኖስ ትወጽእ መርዓት፡፡ ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች” ተብሎ በተነገረው መሠረት ነሐሴ 7 ቀን ተጸነሰች፡፡ ግንቦት አንድ ቀን ሊባኖስ በምትባል ወረዳ በብጽዓት እንደተወለደች የቤተክርስቲያን ታሪክ በሰፊው ያስረዳል፡፡ በጾም በጸሎት በአስተብቁኦት የተገኘች ናት፡፡ ንጽሕት በመሆኗም ማኅደረ እግዚአብሔር ሆናለች፡፡እመቤታችን ከእናትና ከአባቷ ዘንድ ሦስት ዓመት፣ በቤተ መቅደስ 12 ዓመት፣ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ 33 ዓመት ከሦስት ወር፣ ከዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ ዘንድ 14 ዓመት ከዘጠኝ ወር ጠቅላላ ድምር 64 ዓመት ሲሆናት ጥር 21 ቀን በ49 ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡


ነቢያት አስቀድመው ስለ እመቤታችን እረፍትና ትንሳኤ በምሥጢር ተናግረዋል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙር መዝ 136 ፡ 8 “አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ብሉአል፡፡ ፈጣሪዬ ሆይ ምእመናንን ወደ ምታሳርፍበት ወደ መንግሥተ ሰማያት የመቅደስህን ታቦት ድንግል ማርያምን ይዘህ ተነሥ ሲል ነው፡፡ ይህም እመቤታችን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ መነሣቷን የሚያመለክት ነው፡፡ ታቦት ያላትም ማደሪያው ስለሆነች ነው፡፡ • ጠቢቡ ሰሎሞን “ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ እነሆ ክረምት አለፈ ዝናቡም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፡፡ የዜማም ጊዜ ደረሰ የቁርዬውም ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጐመራ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፡፡ ወዳጄ ሆይ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነይ” ሲል ስለ እመቤታችን በምሳሌ ተናግሮአል፡፡ መኃ 2 ፡10-13

 ወዳጁን ውበቱን ተነሺ ነይ እያለ የተጣራው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ተጠሪዋም እመቤታችን ናት፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ ማለት በስደት በአይሁድ የዘወትር ጠላትነት በልጅዋ መከራና ስቅላት ስምዖን በቤተ መቅደስ እንደተናገረ ልቧ በሀዘን ሠይፍ የተከፈለበት በሀዘን ፍላጻ የተወጋበት የመከራ ክረምት /ወቅት/ አልፎ የክርስቶስ ሕማሙ ፣ ሞቱ፣ ቤዛነቱ ተፈጽሟል፡፡ ትንሣኤው በምድር ላይ ተገልጧል፣ ተሰብኳል ማለት ነው፡፡ በምድራችን አበባ ታይቷል ማለት የሐዋርያት ድምፅ በምድር ሁሉ ደርሷል ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ ብሎ ስለ ሐዋርያት የተናገረው በዓለም ያለውን መከራ ስደት ሲገልጽ ነው፡፡ /መዝ 18¸4/

የዜማም ጊዜ ደረሰ ያለው የመከራን ጊዜ ነው፡፡ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ በደስታ ይጮሃሉ፣ ይዘምራሉም ተብሏል፡፡ መዝ 14 ፡ 13 የመከር ጊዜ ደረሰ የተባለው መከር የፍሬ ጊዜ በመሆኑ ክርስትና አፍርቷል ማለት ነው፡፡ በለሱ ጐመራ ማለት ደግሞ በጐ ምግባረ ፍሬ ሳያፈሩ የነበሩ ሰዎች በጐ ምግባር መሥራት መጀመራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በመጨረሻም ወይኖች አብበዋል፣ መዓዛቸውንም ሰጥተዋል እንደተባለ ።በመላው ዓለም አብያተ ክርስቲያናት በሃይማኖት ማበብ መዓዛ ምግባራቸውን ማቅረብ ከጀመሩ በኋላ እመቤታችን አረፈች፡፡

እመቤታችን ጥር 21 ቀን እረፍት በሆነበት እለት ሐዋርያት የእመቤታችንን ሥጋ ለማሳረፍ ወደ ጌቴሰማኒ መካነ እረፍት ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንዓት መንፈስ ተነሣሥተው “ቀድሞ ልጅዋን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሳ፡፡ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል፡፡ እያሉ በማስተማር ሕዝቡን ፈጽመው ወስደውታል፡፡ አሁን ደግሞ ዝም ብለን ብንተዋት እርሷንም እንደ ልጅዋ ተነሣች አረገች እያሉ በማስተማር ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን; ኑ ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጥተው ከመካከላቸው ታውፋኒያ የተባለው ጐበዝ አይሁዳዊ ተመርጦ ሄዶ የእመቤታችንን ሥጋ የተሸከሙትን አልጋ ሽንኮር ያዘ፡፡ የአልጋውን ሽንኮር በያዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሠይፍ ሁለት እጁን ስለ ቆረጣቸው ከአልጋው ሽንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ፡፡

ታውፋንያ በፈጸመው ድርጊት ተጸጽቶ ወደ እመቤታችን ስለተማጸነ በኅቡእ ተዓምር የተቆረጡ እጆቹን እንደ ቀድሞ አድርጋ ፈውሳዋለች (ስንክሳር ዘጥር፡፡) የእግዚአብሔር መልአክ የእመቤታችን ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ተድላ ደስታ ወደ አለባት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቁ፡፡ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው፡፡ እነርሱም ትወጪ ዘንድ እግዚAብሔር አዞሻል አሏት፡፡ ያን ጊዜም ከእፅ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን የማርያም ሥጋዋ ወጣ፡፡ ጌታችንም ዘላለማዊ ወደሆነ መንግሥተ ሰማያት መላእክት እና ሰማእታት እየሰገዱላት አሳረጓት፡፡ ንጉሥ ዳዊት “በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” እንዳለ፡፡ መዝ 44 ፡ 9

ወንጌላዊ ዮሐንስም ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ተመልሶ ከሰማይ ወረደ፡፡ ሐዋርያት ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ሥጋ ፈጽሞ ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው፡፡ እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋም በታላቅ ክብር ማረጉን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ፡፡ የነሐሴም ወር በባተ /በገባ/ ቀን ዮሐንስ እንዲህ አላቸው፡፡ የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት ኑ፤ ሁለት ሱባኤ በመጾም እንለምን አለ፡፡ በጾም በጸሎት ሱባኤ ያዙ፤ ጌታም የእመቤታችንን ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴና በጽኑ ምሕላ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ እረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡

የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዓት በተፈጸመ ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ቶማስ አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጅዋ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡ ትንሣኤዋን ሌሎቹ ሐዋርያት አይተው ለእርሱ የቀረበት መስሎት ተበሳጭቶ “በመጀመሪያ የልጅሽን ትንሣኤ አሁን ደግሞ የአንቺ ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ” ብሎ ከማዘኑ የተነሣ ከደመናው ተወርውሮ ሊወድቅ ቃጣው፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ በቀር ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤዋን እንዳላዩ ነግራው አጽናንታው ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ምልክት ይሆነው ዘንድ ሰበኗን - መግነዟን ሰጥታው አረገች፡፡

ሐዋርያው ቶማስም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንዴት ይሆናል?” አላቸው፡፡ “ አንተ እንጂ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንምን;” ብለው በቅዱስ ጴጥሮስ መሪነት ወደ እመቤታችን መካነ መቃብር ይዘውት ሄደው መቃብሩን ቢከፍቱ ሥጋዋን አጡት፡፡ ደነገጡም፡፡ ቶማስም “አታምኑኝም ብዬ እንጂ እመቤታችን ተነሥታ አርጋለች”ብሎ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፡፡ ለማረጋገጫ ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ ሰበኗን - መግነዟን ለበረከት ቆራርጠው ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄደዋል፡፡

ሐዋርያትም ትንሣኤሽን ቶማስ አይቶ እኛ እንዴት ይቀርብናል ብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ሱባኤ ገቡ፡፡ በሱባኤው መጨረሻ በነሐሴ አሥራ ስድስት ቀን ጌታችን ጸሎታቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ ረዳት ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሰናይ ዋና ዲያቆን አድርጐ ቀድሶ ሁሉንም ከአቆረባቸው በኋላ የእመቤታችንን እርገቷን ለማየት አብቅቷቸዋል፡፡ • ቤተክርስቲያናችንም ሥርዓት ሠርታ ከሰባቱ ዓበይት አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መግለጫ ጾም እንድንጾም አድርጋናለች፡፡ ሐዋርያት ያዩትን ድንቅ ምሥጢር የእመቤታችንን ትንሳኤና እርገት ለማየትና ከሐዋርያት አበው በረከት ለመሳተፍ ጌታችን “ልጆቼ” ይላቸው ለነበሩ ሐዋርያት አምሳል ሕፃናትና ወጣቶች፣ ሴቶችና ወንዶች፣ አረጋውያንም የጾመ ፍልሰታን መድረስ በናፍቆት እየጠበቁ በየዓመቱ በጾም በጸሎት ያሳልፉታል፡፡

የእመቤታችን ትንሣኤና እርገት መታሰቢያ - በጾመ ፍልሰታ  ወቅት ብዙዎች ከቤታቸው ተለይተው በመቃብር ቤት ዘግተው፣ አልጋና ምንጣፍ ትተው፣ በመሬት ላይ ተኝተው ዝግን ጥሬ እፍኝ ውኃ እየቀመሱ በጾምና በጸሎት በመትጋት በታላቅ ተጋድሎ ይሰነብታሉ፡፡ በሰሙነ ፍልሰታ ምእመናን ለእመቤታችን ያላቸውን ጽኑና ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩበት ነው፡፡ጌታችን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር ቆይቶ ሙስና መቃብር ሳያገኘው፣ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በሥልጣኑ እሑድ በመንፈቀ ሌሊት እንደተነሣ ሁሉ እርሷም በተቀበረች በሦስተኛው ቀን ማኅደረ መለኮት ናትና ሙስና መቃብር ሳያገኛት መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል የልጅዋ ሥልጣን ኃይል ሆኗት መነሣቷን ትንሣኤዋ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ እንደ ልጅዋ ትንሣኤ” ነው ተብሎ ሲከበርላት ይኖራል፡፡

በዚሁ በነሐሴ 16 ቀን የሰማእቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፍልሰቱ ነው፡፡ ሥጋው ከፋርስ ሀገር ወደ ሀገሩ ወደ ልዳ በክብር የፈለሰበት ነው፡፡ ፍልሰቴን ከፍልሰትሽ አድርጊልኝ፣ ብሎ ለምኗት ስለነበር ፍልሰቱ ከእመቤታችን ፍልሰት ጋር እንዳሰበው ሆኖለታል፡፡ ስለዚህም እርሷን መውደዱ የሚያውቁ ሥእሉን ከሥእሏ አጠገብ ይስላሉ፡፡ በስሙ ለሚማጸኑ የድኅነት ወደብ ይሆን ዘንድ፡፡

የእመቤታችን አማላጅነቷ አይለየን አሜን፡፡ 

No comments:

Post a Comment