Tuesday, May 08, 2018

ከተኩላዎች መሃል

በንፁህ  መነጽር ማስተዋል ለቻለ፣
ለአቤል  መስዋዕትነት  ቢላው  የተሳለ፣
ከተኩላዎች መሃል ንጹህ  በግም አለ።
እርም አርጎ ትቶ ጥንብን  ለጥንብ አንሳ፣
ወደ ላይ ለመምጠቅ ክንፉን የሚያነሳ፤
ብቻውን  የሚኖር በጆፌዎች መንደር፣
ለአመነበት ጉዳይ የማይደራደር፤
ስለ ድንቅ ብቃቱ  ብዙም ያልተባለ፣
በቁራዎች ሰፈር ነጭ ንሥር አለ።
ይውጠው  ይመስል  ድንቁርናን ቁጣ፣
አባት ለገደለው የልጅ ልጅ ሲቀጣ፤
ቀድሞ ሰው መሆኑን አውቆ የተረዳ፣
ታናናሾቹ  ላይ  ደርሶ   ማይፈነዳ፤
አውቆ ለማሳወቅ ሁሌም  የሚተጋ፣
በጎሜ በነገር  ሰውን  የማይወጋ፣
ከእግዜር  የተቸረ በፀጋ ላይ ፀጋ፤
ስሜትን  የሚያድስ የጥርሱ  ፈገግታ፣
ሰው  አየሁ  በህልሜ ትላንትና   ማታ።
ገጾች  ስገለብጥ  በህልሜ  መዳፍ ላይ፣
እንደዚህ የሚል  ቃል ይነበባል  ከላይ፤
እንደ ሣተኖቹ አንተም ሁን  ሣተና፣
እኩል  የፈጠረህ  የአዳም  ዘር  ነህና።

Ped OPD ይካቲ 17/2010 ዓ.ም ከሌሊቱ 7:30 ተፃፈ

No comments:

Post a Comment