ከሁሉ አስቀድሜ በዚች አጭር ጽሑፍ ቢሆን
ጥሩ ነው ብዬ የማስበውን ሀሳብ ለማስተላለፍ እንጅ አንዱን አሳንሶ ሌላውን
ከፍ የማድረግ ዓላማ እንደሌለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ። ምናልባት መስሎ የሚታየው ካለ ግን እርሱ አስተሳስቡን ያስተካክል።
ያ ስሙን የማላስታውሰው መዝገበ ቃላት
“ስብሰባ የሚለው ቃል በቁሙ ሲፈታ ውኃ ውኃ የሚሉ ሰዎች ተመራርጠው
የሚሰባሰቡበት፤ በየደቂቃው አፋቸውን በሀይላንድ ውኃ እየተጉመጣመጡ ውኃ የማያነሳ ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩበት ፤ በመጨረሻም ከውኃ
የቀጠነ ውሳኔ አሳልፈው የሚለያዩበት የሰዎች ጥርቅም ነው ” ያለው እውነቱን ሳይሆን አልቀረም። እንደዚህ የምለው ያለ ምክንያት
አይደለም፤ ላለፉት አራት ዓመታት እንዳስተዋልሁት ክረምት በመጣ ቁጥር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተባለ የተለያዩ ስብሰባዎች (ስልጠናዎች)ተዘጋጅተዋል ተካሂደዋልም። አንዳቸውም ግን የህክምና
ተማሪዎችን አሳትፈው አያውቁም ። ከ“ጥልቅ ተሐድሶ”ው በስተቀር።
“ይህ የሆነው የህክምና ተማሪዎች ጊዜ
ስሌላቸው ነው።” ብሎ የሚከራከር የዋህ ይኖር ይሆናል። እኔ ግን አይመስለኝም። የስብሰባው አስፈላጊነት ከታመነበት በስብሰባው መሳተፍ
ያለባቸው ጊዜ ተትረፍርፎባቸው “ክረምቱን በምን እናሳልፈው” የሚሉት ሳይሆኑ ጊዚያቸውን አጣበው የሚጠቀሙት ናቸው። ምክንያቱም በትርፍ
ጊዜው የሚሰበሰብ ሰው ሃሳብ የሚሰጠውም ውሳኔ የሚወስነውም
ትርፍ ጊዜ ስላለው እንጅ አስፈላጊነቱን አምኖበትና ከልቡ አስቦበት
ነው ለማለት ይከብደኛል።
በመሰረቱ ለአንዲት ሀገር እድገት የሚያስፈልገው
ሥራ ነው እንጅ ስብሰባ ነው ብዬ አላምንም። የግድ ስብሰባ ያስፈልጋል ከተባለ ግን በ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ህክምና ትምህርት ቤት የገቡ ተማሪዎችን ማሳተፍ አማራጭ የሌለው ግዴታ ይመስለኛል።“ከተባለ
ወዲያ እናርገው በፍቅር ጥርስዎን ያውሱኝ ድንቸ ቆሞ አይቅር” እንዲሉ አያቴ ። እውነት ችግሩ የጊዜ ማነስ ከሆነ ሁለት ሳምንት
የሚፈጀውን ስልጠና አጠር መጠን አድርጎ በአራት ወይም በአምስ ቀናት መጨረስ ያማይቻል ሆኖ ነው? ከህክምና ተማሪ ጭንቅላት የሚመነጨውን ሃሳብ መረዳት የሚችል፣
የሚጠይቁትንም ጥያቄ የመመልስ አቅሙ ያለው የስብሰባ መሪ ከተገኘ
ማለቴ ነው።
መቼም እየተደረገ እንዳለው የAnesthesia ተማሪዎች የ”medicine” ተማሪዎችን ወክለው ይወስኑ
ብሎ የሚሟገት ይኖራል ብዬ አላስብም።
©ጌች ቀጭኑ ነሐሴ 2/2009 ዓ.ም