አንዳንዴ ችግሮች ሁሉ በሰው ላይ ያድማሉ። የመጀመሪያው ችግር ያስከተለው ሃዘንና መከራ ከልብ ሳጠፋ ሁለተኛው ይከተላል። መከራ መከራን እየመዘዘ በመሳሳብ የተቀባዩን አሳርና ፍዳ ያበዛዋል። ጊዜና ምክንያት ተረዳድተው የችግር ሰንሰለት፣የመከራ ቀለበት ይፈጥራሉ። በሰንሰለቱ የታሰረ በቀለበቱ የታጠረ እዬዬን ዘፈኑ አድርጎ ብሶትና ትካዜን ሲያንጎራጉር ተስፋ ቆርጦ ተስፋን እያበቀለ ጊዜ ያመጣበትን ጊዜ እስኪያስረሳው አካል መንፈሱ ይንገላታል። አንዳንዱ ሃዘንና ችግሩን አፍ አውጥቶ ለሌላው በማካፈል አልቅሶ ይለቀስለታል፤አዝኖ ይታዘንለታል። ያም ብቻ ሳይሆን ከከንፈር መምጠጥ አንስቶ እስከ ከባድና ውስብስብ ደረጃ ያለ እርዳታና መፍትሄ ሁሉ ይለገሰዋል። እናም ትንሽ ሲነካ ብዙ በመጮህ ችግሩ ሳይጎዳው በፊት የቅርብ የሩቅ ወዳጁን አስቸግሮ በእንጭጩ ይቀጨዋል። አንዳንዱ ደግሞ ለዚህ አልታደለም። ችግሩን ለብቻው አፍኖ በመያዝ ወደ ውስጡ እያነባ መንፈሱን በጭነንቀት እያደቀቀ አካሉን በጥያቄ እስኪያስገምት ይብሰከሰካል። ብዙ ጊዜ ሐሳብና ችግራቸውን ለብቻቸው ይዘው የሚብሰለሰሉ ሰዎች አካባቢያቸውን በስጋት የሚመለከቱ ናቸው ። ፍርሃትና ጥርጣሬ አይለያቸውም ። እምነታቸው በራሳቸው ላይ ብቻ በመሆኑም ችግራቸውን በውስጣቸው አምቀው በይሉኝታ፣በእልህና በመግደርደር አጽናኝ ረዳት ሳያገኙ ጉዳታቸው እያየለና እየከፋ በመሄድ በእነሱ ፍላጎት ሳይሆን በችግራቸው ከአቅም በላይ መሆን ይጋለጣሉ። ነገር ግን ከረፈደ ነውና ከዘመድ ወዳጅ ሊያገኙ የሚችሉት እርዳታ ችግራቸው የሚወገድበትን ሳይሆን ችግራቸውን አምነው የሚቀበሉበትን ምክርና መፍትሔ ነው። ይህ ጽሑፍ ገመና የተሰኘ ረዥም ልብወለድ ሳነብ ያገኘሁትና በማስታወሻ ደብተሬ ከትቤ ያስቀመጥሁት ሲሆን በዛሬው እለት አንዲት የፌስቡክ ጓደኛዬ “ዛሬ ባጣም ክፍት ብሎኛል“ ብላ ፖስት ስታደርግ ከጠቀማት ብዬ ልኬላት በጣም እንደወደደችው ስለገለጸችልኝ በጦማሬ ላይ ላሰፍረው ተገድጃለሁ።ጥሎብኝ ሴት ልጅ ስትከፋ ማዬት አልወድም።
No comments:
Post a Comment