በአፍላ ትጀምራላችሁ በወረት ትተውታላችሁ። ያወቃችሁትን ትረሳላችሁ ያላወቃችሁትን ለማወቅ ትጥራላችሁ፤የያዛችሁትን ትረግጣላችሁ፤የረገጣችሁትን ትይዛላችሁ፤ምኞታችሁ ልክ የለውም፤አምሮታችሁ ብዙ ነው።የአማራችሁን ስታገኝ ወዲያው ይሰለቻችኋል።ተው የተባላችሁትን ትሽራላችሁ የተከለከላችሁትን ትደፍራላችሁ፤የተፈቀደላችሁን ችላ ትላላችሁ።ቤተመቅደስ እንዳትገቡ ብትከለከሉ ወደ ፊት ቤተመቅደሱን በመስታውት ሰራታችሁ
ቤተመቅደስ ባትገቡም እንኳን ሁሉን ከወጭ ሆናችሁ ማየት ትፈልጋላችሁ።ሁሉንም ማወቅ ትፈልጋላችሁ በአንዱም ግን
አትጠቀሙበትም።ሁሉም አላችሁ ግን ባዷችሁን ናችሁ።ሃይማኖት እንጅ እምነት የላችሁም።
መድሃኒት ባሳይህ መቀመሚያውን ነገሬህ ማርከሻውን ሳልገልጥልህ መጀመሪያውን ብቻ ሞጭልፈህ ትተኸኝ ትሄዳለህ።ጥበበን "ሀ ግእዝ "ብየ ላስተምርህ ብሞክር መንደር ውስጥ በቃረምካት እውቀትህ ተመክተህ በመሰላቸት "ሆ ሳብዕ" ብለህ ቀድመህ ትዘጋዋለህ። የግል ታሪካችሁ ቢታይ ወጥነት የጎደለው ከዚህም ከዚያም የተልከፈከፈ የተማሪ ኮፈዳ ውስጥ ያለ እህል ይመስላል።ተምራችሁ እውቀት ስታገኙ ሰርታችሁ ገንዘብ ስታፈሩ ከላይ የሆናችሁበትን ሃገር ለቃችሁ "ሰፋ ወዳለው እንሂድ" ብላችሁ እንደገና ከታች ትጀምራላችሁ።ትቀጥላላችሁ በመጨረሻ ከጀመራችሁበት ትገኛላችሁ ።ቸኩላችሁ ትወስናላችሁ ወዲያው ትጸጸታላችሁ።በጽኑ ታማችኋል።