Friday, June 05, 2015

የነፍስ እና የስጋ ቡጢ

ጊዚያችን ካለፈ እንዳይቆጨን ኋላ፣
እንዝፈን አንዝፈን እንጹም እንብላ፣
እንስጥ እንቀማ እየተባባሉ፣
ነፍስ እና ስጋየ በፈቃድ ተጣሉ።
የሚያስታርቃቸው ሽማግሌ ጠፍቶ ፣
ደግሞ ላይስማሙ ጠባቸው ጎርንቶ።
በስድሳ ዙር ቡጢ ደግሞ በሰማኒያ፣
እጅግም ቢበዛ መቶ መቶ ሃያ፣
ቆርጠው ሊፋለሙ ተፈላለጉና፣
ወደ ሜዳ ገብተው ባንድ ላይ ቆሙና፣
ለየደጋፊያቸው ንግግር ሲኣደርጉ፣
ስጋ ብቻ ነበር የሚታይ በወጉ።
ከመድረኩ ቆሞ ስፎክር ሲያገሳ፣
ማን እንደሱ ጀግና ማን እንደሱ አንበሳ።
ነፍስ ግን በፍርሃት እንደሌለች ሆና፣
ደጋፊወቿንም እጅግ አሳዝና፣
ትታይ ነበረ ገርጥታ ኮስምና።
ዳኛው ፊሽካ ነፍተው ሲጀመር ያ ጣጣ፣
ስጋ ተንደርድሮ ሊያቀምሳት ሲመጣ፣
ነፍስ አሳለፈችው አቅጣጫ ለውጣ፣
ቁጭ ብድግ ብላ ሩጣ ተራውጣ።
ልትዘል ስትሞክር በስተኋላ ዙሮ፣
ሰንጎ ያዘና የነፍስን ጉሮሮ፣
ሲያጣድፋት ጊዜ በእርግጫ በጡጫ፣
በስተሃያኛው ዙር አጣች በግቢያ መውጫ።
የነፍስ ደጋፊዎች ሲያዝኑ ሲሳቀቁ፣
ዳኛው ስጋን ገፍተው ነፍስን አስለቀቁ።
ጉሮሮ በማነቅ ፋውል በመስራቱ፣
ስጋን ተቆጥተው መከሩ ዘበቱ።
መላ ቅጥ ቢያሳጣት የሥጋ ጨዋታ፣
እንደማያዋጣት መዝና ገምታ፣
በግርግር መሃል ባገኘችው ፋታ፣
ነፍስ ሾልካ ጠፋች ፉክክሩን ትታ።
አሸናፊነቱ ጀግንነቱ ታውቆ፣
አስጨንቆ ይዞ ሳያስቀራት አንቆ፣
ታታው እነድሄደች ስጋ ይህን አውቆ፣
ያለቅስ ጀመረ ተዝለፍልፎ ወድቆ፣
አይን ጥርሱ ገጦ አረፋን አድፍቆ።
በሀዘን በለቅሶ እራሱ ፈረሰ፣
አመድ ነሰነሰ በአፈር ተለወሰ።
እንዲያ ሲደነፋ ሲዘል የነበረ፣
ከመድረኩ መሃል ስጋ ወድቆ ቀረ።
              ምንጭ፦ ከሰይጣን ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ እና ሌሎች

No comments:

Post a Comment