Friday, June 05, 2015

የነፍስ እና የስጋ ቡጢ

ጊዚያችን ካለፈ እንዳይቆጨን ኋላ፣
እንዝፈን አንዝፈን እንጹም እንብላ፣
እንስጥ እንቀማ እየተባባሉ፣
ነፍስ እና ስጋየ በፈቃድ ተጣሉ።
የሚያስታርቃቸው ሽማግሌ ጠፍቶ ፣
ደግሞ ላይስማሙ ጠባቸው ጎርንቶ።
በስድሳ ዙር ቡጢ ደግሞ በሰማኒያ፣
እጅግም ቢበዛ መቶ መቶ ሃያ፣
ቆርጠው ሊፋለሙ ተፈላለጉና፣
ወደ ሜዳ ገብተው ባንድ ላይ ቆሙና፣
ለየደጋፊያቸው ንግግር ሲኣደርጉ፣
ስጋ ብቻ ነበር የሚታይ በወጉ።
ከመድረኩ ቆሞ ስፎክር ሲያገሳ፣
ማን እንደሱ ጀግና ማን እንደሱ አንበሳ።
ነፍስ ግን በፍርሃት እንደሌለች ሆና፣
ደጋፊወቿንም እጅግ አሳዝና፣
ትታይ ነበረ ገርጥታ ኮስምና።
ዳኛው ፊሽካ ነፍተው ሲጀመር ያ ጣጣ፣
ስጋ ተንደርድሮ ሊያቀምሳት ሲመጣ፣
ነፍስ አሳለፈችው አቅጣጫ ለውጣ፣
ቁጭ ብድግ ብላ ሩጣ ተራውጣ።
ልትዘል ስትሞክር በስተኋላ ዙሮ፣
ሰንጎ ያዘና የነፍስን ጉሮሮ፣
ሲያጣድፋት ጊዜ በእርግጫ በጡጫ፣
በስተሃያኛው ዙር አጣች በግቢያ መውጫ።
የነፍስ ደጋፊዎች ሲያዝኑ ሲሳቀቁ፣
ዳኛው ስጋን ገፍተው ነፍስን አስለቀቁ።
ጉሮሮ በማነቅ ፋውል በመስራቱ፣
ስጋን ተቆጥተው መከሩ ዘበቱ።
መላ ቅጥ ቢያሳጣት የሥጋ ጨዋታ፣
እንደማያዋጣት መዝና ገምታ፣
በግርግር መሃል ባገኘችው ፋታ፣
ነፍስ ሾልካ ጠፋች ፉክክሩን ትታ።
አሸናፊነቱ ጀግንነቱ ታውቆ፣
አስጨንቆ ይዞ ሳያስቀራት አንቆ፣
ታታው እነድሄደች ስጋ ይህን አውቆ፣
ያለቅስ ጀመረ ተዝለፍልፎ ወድቆ፣
አይን ጥርሱ ገጦ አረፋን አድፍቆ።
በሀዘን በለቅሶ እራሱ ፈረሰ፣
አመድ ነሰነሰ በአፈር ተለወሰ።
እንዲያ ሲደነፋ ሲዘል የነበረ፣
ከመድረኩ መሃል ስጋ ወድቆ ቀረ።
              ምንጭ፦ ከሰይጣን ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ እና ሌሎች

Tuesday, June 02, 2015

ሰሳ


Yaya-Sanogo
በአንድ የክረምት ወራት ዝናብ እንዳባራ፣
ወጣ አልኩኝ ከቤቴ ቀለል ላለ ስራ።
በጠራው ሜዳ ላይ አንድ የሜዳ ሰሳ፣
አየሁ ሰርዶ ልትግጥ ስትወድቅ ስትነሳ።
አወ ራራሁላት ችግሯን አይቼ፣
ፈለግሁ ልመግባት ከስርዶው ነጭቼ።
ከአጠገቧ ሰርዶ ነቃቅየ ይዤ፣
እሥሥ ብይ ብየ ጋበዝኋትኝ በእጄ።
ጥላኝ ስላልሮጠች አልቆረጥሁም ተስፋ፣
እሷም ቀጥ እኔም ቆምሁ ፍጥጫው ተስፋፋ፣
ከመካከላችን እግር ነቃይ ጠፋ።
ካሰብሁኝ በኋላ አውጥቸ እና አውርጄ፣
ወሰንሁኝ ልሰጣት እኔው ግፋኝ ሂጄ።
አንድ እግሬን አንስቼ ወደ ፊቴ ስጥል፣
እሷም የኋላ እግሯን የኋሊት ስትነቅል።
የግራውን እግሬን ሳነሳው ለአንድ አፍታ፣
እሷም ሸርተት ስትል የኔን እግር አጥታ።
ስትሄድ ወደ ኋላ እኔም ስከተላት፣
በጨበጥሁት ሰርዶ ስጥር ላባብላት፣
ወደፊት አምጥቸ ከሳሩ ላበላት።
እሥሥ አንች ሰሳ ሰላም ነኝ አትፍሪ፣
አገሩም ሰላም ነው ሰውንም ድፈሪ፣
አንችም እንደ ሰወች በነጻነት ኑሪ።
ብየ ብቀባጥር አላዳመጠችም፣
አወ አትናገርም አልተናገረችም፣
ከኋላ ጉዞዋም ፈጽማ አልቆመችም።
እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ እርሷም ስትጎትተኝ፣
ሚዳቆች ቡኸሮች ጮቤ እረገጡ፣
ከኋላዋ ካለው ከዱሩ እየወጡ፣
ለጎሪጥ እያዩዋት አልፈዋት እሮጡ።
አፌ ስራ አልፈታምጮሆ ይናገራል፣
ወደፊ ተራመጅ እንደነሱ ይላል።
እየጎተተችኝ በሃሳብ ተውጣ፣
ከስርዶው ልትጎርስ ወደፊት ስትመጣ።
ድንገት ሳታስበው ከጥንት ዘመን ጉድባ፣
ሁለት የኋላ እግሯ ሰርጎድ ብሎ ገባ።
በሁለቱ እግሮቿም ጋማቱን ጨብጣ፣
ሰማሁኝ ለእርዳታ ቃል ከአፏ ሲወጣ።
ጎትቸ ለማውጣት በተቻለኝ አቅሜ፣
ሁለት የፊት እግሯን ያዝሁ ተሽቀዳድሜ።
እየጎተትሁ ሽቅብ አንገቷ ሲወጣ፣
የዝንጀሮ መንጋ ከዋሻው ስር መጣ።
አንዱ አንዱን ረግጦ አንዱ በአንዱ ወጦ፣
አንደኛ ጅራቷን አንዱ እግሯን ጨብጦ።
ያን የገደል ዋሻ ተቆላልፈው ወጥተው፣
ፈለጉ ሊወስዷት ከመዳፌ አውጥተው።
ምን ሊያደርጋት ይሆን የዝንጀሮ መንጋ፣
ከመቸስ ወዲህ ነው የለመደው ስጋ።
ብየ እየጎተትኋት ወደታች ባፈጥ፣
የተራበ አንበሳ አየሁኝ ከዉስጥ።
እኔም ላላስበላት ስጎትት ስትወጣ፣
ጨለማው ተገፎ ታየኝ ቀን ሲመጣ፣
እኔ ብቻ ነቃሁ ሕልሜ ትርጉም አጣ።

የሌሊት ዜማዎች

ተዋናይ ነው አሉ፣
ሞትን የገዘተ ሰባት አመት ሙሉ።
ታዲያ ምን ይደንቃል፣
እንቅልፍን ገዘትሁት እኔ በምስኪን ቃል።
የእድሜወቼን እሸት ቢበላ ቢበላ፣
አሲዳም እንቅልፌ መቼም ከርሱ አይሞላ፣
መደቤን አፍርሼ ከህልሜ ልጣላ።
ተዋናይ ስለምን አምላክን ይከሳል፣
ሞት አንዴ ይመጣል ህልም ይመላለሳል።
መቃብርን ደፍኖ ሞትን በቁም አስሮ፣
ሰው ነፍሱን ይቀብራል ሕልሞቹን ቆፍሮ።
ተዋናይ ምርኮህን ልቀቀው ይፈታ፣
ና! እንቅልፍን እሰር በሞት እግሮች ፈንታ።
በአልጋ እቅፍ ለኖረ ጉድጓድ መች ይከብዳል፣
ከመቃብር ይልቅ ሕልም ይጎደጉዳል።

ገንዘብ

10624745_1730988887125730_7825557555215847685_n
ፍሬ መሬት ወድቆ ከዋለ ካደረ፣
ገንዘብ ሰውን ገዝቶ መቅበር ከጀመረ፤
የመጣ ነውና ቀድሞውን ከጥንት፣
ሁለቱም አይድኑም ከመበላሸት፤
ገንዘብ መፈጠሩ ለሰው አገልጋይ፤
ሆኖ ሊሰራበት አልነበረም ወይ?
አሁን ግን መስገብገብ በጣም ስለበዛ፣
ሰው ባሪያ እየሆነ ለገንዘብ ተገዛ።
ለስሙ ስም አለን ከጥንት እስከ አሁን፣
በእምነታችን ኗሪ ሟች ለክብራችን፣
በማጣት ተወልደን በንጣት አድገን፣
ለገንዘብ እጅ ሰጠ ኩሩልባችን።

መሽቷል አትበል

በውድቅቱ አትከፋ
በጎህ መቅደድ አትጽናና፣
ብርሃን ለመመፅወት አትበል ቀና፣
የእኛ ፀሐይ ሐሩር እንጅ ብርሃን አትወልድምና።
መሽቷል አትበል ጀንበር ስትጠልቅ
ከዛጎሏ ውስጥ ገብታ፣
መሽቷል አትበል ፀሐይ ስትሞት
በከዋከብት ተተክታ፣
በውስጥህ ላለው ብርሃን
ግርዶሽ የሆንህ ለታ፣
ያን ጊዜ ሆኗል ጽልመት
ያን ጊዜ ሆኗል ማታ።
          ስብስብ ግጥሞች ፦በውቀቱ ስዩም