ይህች ሀገር ብዙ የተከፈለባት ምድር ናት! ለውድቀቷ የተጉ የመኖራቸውን ያህል፣ ብዙዎች ሕይወታቸውን ከፍለው
ለዛሬ ያበቋት ሀገር ናት፡፡… እኒህ ባለውለታዎቿ ሰው እንደመሆናቸው፣ የሰው ልጅ በዘመኑ የሚፈጽመውን ስህተት
የፈጸሙ ቢሆን እንኳን፣ እናት ላሏት ኢትዮጵያ የከፈሉት ዋጋ ከዋጋ በላይ ነው፡፡ ይህንን መካድ፣ አለማክበርና
ማባከን አለመታደል ነው፡፡ ራስንም ለውርደት አሳልፎ መስጠት! ስለዚች ሀገር ነጻነትና ክብር ብዙዎች በብዙ
መልኩ ደክመዋል፡፡ መከፋታቸውን ችለውና ከራሳቸው ሀገራቸውን አስቀድመው ስለ እሷ ታትረዋል፡፡ በክፉ ቀንም
አንገታቸውን ለሰይፍ፣ እግራቸውን ለጠጠር፣ ደረታቸውን ለአረር ሰጥተው ስለ ክብሯ ወድቀዋል፡፡ “የዛሬን
አያድርገውና” ለኢትዮጵያውያን ስለ ሀገር ክብርና ስለ ሕዝቦች ነጻነት ሕይወትን መክፈል ታላቅነት ነበር፡፡ በዚህ
አብዝታ የተመካችው ንግሥት ጣይቱ፤ አያውቀንም ላለችው የኢጣሊያ መንግሥት ወኪል አንቶኔሊ እንዲህ ነው ያለችው፡-
“… የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፡፡ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሀበሻ ጌጡ ነው፡፡ ሂድ ባሻህ ጊዜ ተመለስ ተሰናድተን
እንጠብቅሃለን፡፡”ይህች ሀገር ዛሬ ላይ የደረሰችው ብዙ ዋጋ ተከፍሎባት ነው፡፡ ከክፍያም በላይ የሕይወት
ዋጋ ተከፍሎባት፡፡ በዚህም አባቶቻችን እኛን አልፎ የአፍሪካውያንን አንገት ከተደፋበት ቀና ያደረገ፣ ዓለምንም
“አጃዒብ” ያሰኘ አኩሪ ገድል ፈጽመዋል። ይህ ማንም የማያብለው የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ ደረቅ ሀቅ!
ያም ሆኖ
ታላላቅ ገድሎቻችንን ልናከብራቸውና ልንማርባቸው ሲገባ፣ ከንቱ እጅ እንደገባ ወርቅ ሁሉ አልባሌ ቦታ ተትተውና ቸል
ተብለው ባክነዋል። ድሎቻችን ወደ ፊት መስፈንጠሪያችን ሊሆኑ ሲገባ ግብ የለሽ የቸከ ተረት አድርገናቸዋል። ድሎቹ
የሰጡንን መነቃቃትና አቅም ከድርጊት ይልቅ በመተረት እናባክናለን፡፡ ለዘመናት እየሆነ ያለው ይኸው ነው፡፡ እውነቱን
መቀበል ቢገደንም ቅሉ፣ እየሆነ ያለው እንዲሁ ነው፡፡ ድሎቻችንን ለዘመናት አባክነናል፡፡ አሁንም ለመማር ዝግጁ
አንመስልም። በዓለም የነጻነት ታሪክ ውስጥ እንደ ተአምር ከሚቆጠሩት ክስተቶች አንዱ የሆነው አንጸባራቂው የአድዋ
ድልም እንዲሁ ከዚህ መባከን አላመለጠም።… አድዋ! ስለ አድዋ ድል በየጊዜው የሚባለውን ሰብስበን እንበለው፡፡
የአድዋ ድል ነጮች የጥቁር ህዝቦች የበላይ ነን ብለው ለዓመታት ቀንበራቸውን ባጸኑበት፣ ጥቁሮችም ይህንኑ አምነው
ለዘመናት በተገዙበት ዘመን ሀበሾች በነጮች ላይ የተቀዳጁት አንጸባራቂ የነጻነት ድል ነው፡፡… ይህ ክስተት የዓለምን
አስተሳሰብ ቀይሮአል፡፡ እንኳንም በባርነት ቀንበር ተቀይደው የነበሩትን ጥቁሮች ቀርቶ የቅኝ አገዛዙ ተዋናዮቹን
ሳይቀር እምነታቸውን አስፈትሾአል፡፡



