Saturday, February 25, 2017

ክራርና ፍቅር











{{ኤፍሬም ስዩም}}
ትግስት በሌለባት በጨከነች ሌሊት፣
ወዳጅ ለወዳጁ ደብዳቤ ጻፈላት።
ከመጽፉ በፊት!
ከጥቁር ሰማይ ላይ ሦስት ኮከቦች አዬ፣
ለጥቂት ቅፅበታት ከከዋከብቱ ላይ ሀሳቡን አቆዬ።
አንደኛዋ ኮከብ እጅግ የደመቀ ብርሃን ትረጫለች፣
ሁለተኛዋ ግን ደመቅ ትላለች ከአንዷ ትሻላለች፣
ሦስተኛዋ ደግሞ እርሱን ትመስላለች፣
በሁለቱ መካከል ፈዝዛ ትታያለች።
እርሱን ለምትመስለው ብዕሩን አነሳ፣
ሁለቱን ከዋከብት ልቡናው ረሳ፣
አሁንም ዳግመኛ ከመጻፉ በፊት!
ከአንድ አመት ቀድሞ 
በእሷ የተጻፈ ደብዳቤዋን አዬው፣
የደብዳቤው ሀሳብ የደም እንባ አስነባው፣
እንባው ማፍቀሯ ነው መፈቀሩም እንባው፤
የሀሳቧም ሀሳብ
ለሁለት ዘላለሞች አፈቅርሃለሁ ነው።
በትንሹ ታምኖ ብዙ ያልወደደ፣
ስለተፈረቀም ትንሽ ካላበደ፣
በትንሽ እምነቱም ያልተወላገደ።
ፍቅርን እንዴት ያውቃል?
እንዴት ይረዳዋል?
ምን ነበር የጻፍሽው?ምንድን ነበር ያልሽው?
የሆነ መስመር ላይ
አስተውለው ብለሽ ከታች ያሰመርሽው፤
ፊደል እስኪጠፋው እጁን ያሰርሽበት፣
የፍቅር ቀለማት  የማይጠፉ ቃላት፣
የእውነት መገነዣ ሌላ የአንቺ እውነት፤
የአንቺ እውነት ፍቅር፣
የእርሱ ፍቅር ፊደል፣
ካፈቀረስ በቀር ፍቅርን ማን ይገልጻል?
ማንበብ ክፉ ነገር መጻፍ መገላገል፣
ይህ አይደል መታደል።
ምን ነበር የጻፍሽው?ምንድን ነበር ያልሽው?
አስተውለው ብለሽ
የሆነ መስመር ላይ ከታች ያስመርሽው፤
ይልቅ ያን አስታውሰሽ
የክራሩን ድምፅ አሰሚኝ
የዜማ ድምፅ ከዚያ ይውጣ፣
እኔም ክራሩን ሆኘ ባንቺ ጣት ልቀጣ።
እኔ እና አንቺ እንዲያ ነን፣
በሁለት አንድነት ዝንታለም የታሰርን፣
በቅኝት ሚወጣ ጣትና ክር ነን።
ወይም ድምፅና ክር፣
ፍቅርን ጣት አርገነው በአንድነት ምንዘምር።
ምን ነበር የጻፍሽው ?ምንድን ነበር ያልሽው?
የሆነ መስመር ላይ
አስተውለው ብለሽ ከታች ያሰመርሽው፤
በጻፍሽው መስመር ላይ መብረቅ ፍቅር አለ፣
የዝናብ ድምጽ የለም ደመና ግን አለ።
ከደመናው በፊት የደብዳቤሽ ቃላት፣
አንተ ማለት ባሕር እኔ ማለት ትነት፣
በፀሐይ ፈገግታ ጨውን የምንፈጥራት፤
አንተ ማለት ፀፀት እኔ ማለት መዳፍ፣
የቀደመ እንባህን ከዓይንህ ላይ የምገፍ፤
አንተ ማለት ጥማት እኔ ደግሞ እርካታ፣
በበረሃ ንዳድ የምገኝ ጠብታ፤
ማንበቡን ቀጠለ፣
የመብረቅ ብልጭታ የዝናብ ድምፅ አለ፣
በጥቁር ደመና ቀድሞ የታዘለ።
ደብዘዝ ያለ ብርሃን የማትታይ ፀሐይ፣
የተኳረፈ ፍቅር ያልረገፈ አደይ፣
በሁለታችን አዝኖ የተከፋ ሰማይ፤
ይህ ሁሉ ቢሆንም መዳፍሽ ርቋል፣
ጨውነቱም ጠፍቷል ቃሎችሽ ሰክረዋል፤
በዚያ ታላቅ ዝናብ ምድር ስትቀጣ፣
በመብረቅ ብልጭታ ነፍሳችን ስትወጣ፣
እኮ በምን እግሬ ከደጃፍሽ ልምጣ?
አንቺ እንደሆን ንግሥት የመኳንንት ልጅ፣
ህንፃ ፍቅር ልብሽ ጉብዝናን የሚያስረጅ፣
እኮ በምን ሀይሌ ልርገጠው የአንቺን ደጅ?
ማን በምን ጉልበቱ በዬት ጀግንነቱ
ዝም ባለ ቅጽርሽ ያንቺ ኩርፍያ  ነግሶ፣
ፊትሽን ፍራቻ ልቦናዬ ፈርሶ፣
በሳምንት ዘመንሽ ዓይኔ ደም አልቅሶ፤
እኮ በምን አቅሙ?
እንዴትስ ተደፍሮ ደጅሽ ይረገጣል?
ዓይኑስ እንዴት ደፍሮ
እንባውን ጠራርጎ ያንቺን ዓይን ያያል?
ምን ነበር የጻፍሸው ?ወይስ እኔ ጻፍኩኝ፣
ከፍቅርሽ ላይ ወይን ደብልቄ ጠጣሁኝ።
ፍቅር እና ወይን
የሁለት አንድነቱን የጣትና ክሩን፣
በስልት የተቃኘ ክር ድምፅነትን፤
ፍቅርን ጣት አርገደነው በተነካን ቁጥር፣
በስሱ ከላይዋ እንደተመታች ክር፣
በራሳችን ቃና በራሳችን መዝሙር፣
ለዘላለም ዕድሜ በአንድነት ተገመድን?
ወይስ ምንም ሆንን?
እውነት ምንም ሆንን?
ዜማ ሰጭ ፍቅራችን ተበጠሰ ላላ?
የእኛ ቅኝታችን በእኔነት ተበላ?
ያለ ሞያው ገብቶ፣
ያለመጠን ነክቶ፣
ያለ ስልቱ ቃኝቶ፣
ክራር ፍቅራችንን ክሩን ማን በጠሰ?
በምን ዓይነት ስልትስ ዜማችን ታደሰ?
ከሀሳቡ ነቃ
በራሱ ክር ላይ የራስ ስልቱን ቃኘ፣
ለደብዳቤዋ መልስ ሊመልስ ተመኘ፤
ላንተ ያለችውን ላንቺ ብሎ ጻፈ፣
በራስ የቃል ስልቷ ቃሉን አከነፈ፤
ረስቶት ነበረ! 
ከጠረጴዛው ስር በጽዋ ተሞልቶ ወይን ተቀምጧል
ጥቁር የወይን ደም!
ከጽዋ አንስቶ አንድ ጊዜ ጠጣለት፣
አንዱን ሳያጣጥም ጽዋው ወደቀበት፤
የፈሰሰው ወይን ልብሱን አረጠበው
መሬቱን አራሰው፣
ፍንጥቅጣቂው ደግሞ ዓይኑን አስለቀሰው።
የብርጭቆው ጽዋ አልተሰባበረም፣
ሁሉም ፈስሶበታል የተረፈው የለም።
ለመጻፍ ከበደው፣
ደብዳቤው ቀፈፈው፤
መሬት አጎንብሶ፣
እጁን ተንተርሶ፣
ስለሆነው ሁሉ ያስተውል ጀመረ
“እንቆቅልሽ!”
የወደቀ ጽዋ ያልተሰባበረ፣
የፈሰሰ ወይን በአንድ ጉንጭ የቀረ፣
ያላለቀ ጽሑፍ በረቂቅ የኖረ፣
ያኮረፈች ፍቅር ደጇ የታጠረ፤
አራቱ ምስጢሮች
ሳይተርጎሙ ሳይመረመሩ፣
በአፍቃሪው ልቦና
እንቆቅልሽ ሆነው ለዘላለም ቀሩ።

Saturday, February 18, 2017

ዘመናዊት ጀግና

ከሰማይ ዶፍ ቢወርድ ቢዘንብ መከራ፣
ጠላት ቢያንገራግር ቢፎክር ቢያቅራራ፣
ችግር ቢደራረብ ቢመስል ተራራ፣
ጠብ የሚል ባይገኝ  ከምድር ጎተራ፣
ከአቋሟ የማትወርድ ልቧ የማይፈራ፤
በእምነቷ የጸናች ቃሏ የታመነ፣
ክብሯ ከነገሥታት ልጆች የገነነ፤
በሐሜት በወሬ ልቧ 'ማይሸበር፣
በሰው መጠቋቆም ቅስሟ 'ማይሰበር፣
ነገን የምትጨብጥ ዛሬን ተረግጣ፣
ዘመናዊት ጀግና አብቅሏል ሰቆጣ።

Friday, February 10, 2017

ታቾቹ ተበሉ

ሲለው ካባ ለብሶ፣ሲሻው ካባ አውልቆ፤
ሲሻው አፈር መስሎ፣ሲሻው ተብረቅርቆ፤
ሲሻው ካኪ ለብሶ፣ሲሻው ቁምጣ ታጥቆ፤
ከዘመን ተማስሎ ከበላይ ተጣብቆ፤
ሥሩን እያጠቃ፣ሥርዓቱን ዘልቆ፤
ያልበላው ከበላው፣እየተቃበሉ፤
ሦስት ሺህ ዓመታት ታቾቹ ተበሉ
ኄኖክ ሥጦታው

Thursday, February 09, 2017

Woodrow Wilson

“We grow great by dreams… Some of us let these great dreams die,but others nourish and protect them; nurse them through bad days till they bring them to the sunshine and light which comes always to those who sincerely hope that their dreams will come true.”

Sunday, January 22, 2017

የክርስቶስ ነገር

“የክርስቶስ ነገር እጅግ አስቸገረ። ልጅ ስለሆነ ይሆን? አንድ ጊዜ ተርቤ አላበላችሁኝም ይላል። አንድ ጊዜ አምስት እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው አብልቶ አትርፎ ያስነሳል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ገንዘባችሁን እየሰበሰባችሁ ወደ ሰማይ ላኩ እዚያ ይቆያችኋልና ይለናል። ለካ የእርሱ ገንዘብ አልበቃው ቢል ወደኛ ልጁን የላከ ቀስ ብሎ ገንዘባችንን በብልሃት እንዲያከማች ኖሯል። እንግዲህ አወቅንበት ገንዘባችንንም አናባክንም። ከሰማይስ እኛ ምን አለን? ገነዘባችንን አሸክመን ወደ ዚያ ከምንልክ አንካሶችን እውሮችን ችጋረኞችን ወንድሞቻችን ይዘን እንክት እያደረግነ እንበላዋለን።በገንዛ ገንዘባችን ምን ይመጣብናል። አላመጣችሁም ብሎ የሚያደርገውን እስኪ እናያለን።”
(መጽሓፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ) መልካም ዕለተ ሰንበት!!!

Friday, January 06, 2017

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የወላዲተ አምላክ የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ሁላችሁም እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ። ልዑል እግዚአብሔር ፈጣሪያችን የባሕርይ አምላክ ሲሆን በፍጥረቱ የማይጨክን ርኅሩኅ ነውና ሊያድነን ስለፈቀደ ፍጹም ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዷልና ዛሬ የልደቱን በዓል ለምናከብርባት ዕለት እንኳን አደረሳችሁ። ሱባኤ ከተቆጠረ፣ትንቢት ከተነገረ በኋላ ማለትም ቅዱሳን ነቢያት ይመጣል፣ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ብለው ተናግረው ከጨረሱ በኋላ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን አምላክ ከአንቺ ይወለዳል ብሎ አበሰራትና ጊዜው ሲደርስ ማለትም 5500 ዘመን ሲፈጸም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተልሔም በተባለው  ቦታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ።ኲነኔ፣ፍዳ፣መርገም፣ኀዘንና ኃጢአት ሁሉ ተደመሰሰ ። አንድነት ፣ ስምምነት፣ርኅራኄ፣ሰላምና ፍቅር ሰፈነ። ስለዚህም ዛሬ የምናከብረው ይህንን ታላቅ ዕለት የጌታችንን ልደት ነው። ልደት፦ትርጉሙ ከማኅጸን መወለድ ፣ከእናት ሆድ ወደ ብርሃን መውጣት፣መገኘት፣ተገልጾ መታየት ማለት ነው።         


በአንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ “ፈጽሞ ሰው ሆነ” ሲባል በመጀመሪያ በጽንሰቱ በኋላም በልደቱ አምላክ ወልደ አምላክ በሥጋ መገለጡን ያመለክታል። በድንግል ማኅጸን ሳለ ጥቂት ቅዱሳን ብቻ ያውቁት ነበር፤ ከልደቱ በኋላ ግን ለዓለም ሁሉ ተገለጠ። ሕዝብም አሕዛብም የሚያዩት የሚዳስሱት ሰውነት ያለው ሆኖ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ እንደ ሰው ተገልጧል ። የአሁን አመጣጡ በስጋ በመገለጥ ነው፤ የቀድሞው አመጣጡ ግን በመለኮታዊ እሳት አምሳል ስለነበር ማንም ሊቀርበው አይችልም ነበር። ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መገለጥ በሚታይ በነበልባል ውስጥ ነበር። በእሾህ ቁጥቋጦ መካከል በሚነደው እሳት የተገለጠው አምላክ ለሙሴ ብቻ ነበር። ወደ ተቀደሰውም ቦታ ጫማውን አውልቆ እንዲቀርብ ለሙሴ ተነግሮት፣እርሱም በፍርሃትና በመደነቅ ለምለሙ ቁጥቋጦና ነበልባሉ ተዋሕደው ወደሚታዩበት ኅብረ ትርእይት ተጠግቶ የአምላክን መገለጥ አይቶ የዘላለም ስሙም “ ያለና የሚኖር” እርሱ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እንደሆነ ለማወቅ በቅቷል ዘጻ 3፥1-15 ይህ የብሉይ ኪዳን መገለጥ ነበር።

Wednesday, January 04, 2017

ገና በጎዳና

ሁለት የጎዳና ልጆች የገና ዋዜማ አመሻሽ ላይ፣ ጎዳና ዳር ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚው ለዓመት በዓል ሲራወጥ ያያሉ፡፡ ዶሮ ያንጠለጠለ በግ የሚጎትት፣ ቄጤማ የቋጠረ፣ በሬ የሚነዳ፣ እህል ያሸከመ፣ ‹የገና ዛፍ› የተሸከመ፣ አብረቅራቂ መብራት የጠቀለለ፣ ዋዜማ ሊቆም ወደ ቤተ ክርስቲያን ነጭ ለብሶ የሚጓዝ፣ ምሽቱን በዳንስ ሊያሳልፍ ሽክ ብሎ ወደ ጭፈራ ቤት የሚጣደፍ፣ ብቻ ምኑ ቅጡ፣ ከተማዋ ቀውጢ ሆናለች፡፡ እነርሱ ደግሞ የተበጫጨቀች ልብስ ለብሰው፣ የደረቀ ዳቦ ይዘው፣ በቢል ቦርድ ላይ የተለጠፈውን የጥሬ ሥጋ ሥዕል እያዩ፣ መጣሁ መጣሁ የሚለው የገና ብርድ እያቆራመዳቸው፣ የቆሸሸ ሰውነታቸውን እየፎከቱ፣ የቀመለ ፀጉራቸውን እያከኩ፣ በታኅሣሥ 15ና በታኅሥ 29 መካከል ያለው ልዩነት ጠፍቷቸው፣ የበግ ድምጽ እንጂ ሥጋው ርቋቸው፣ የበሬው ፎቶ እንጂ ሥጋው ጠፍቶባቸው፣ ያገኙትን ወረቀት እያነደዱ ጎዳናው ዳር ተቀምጠዋል፡፡

‹‹ቆይ ግን ገና ምንድን ነው?›› አለ አንደኛው ሰውነቱን እየፎከተ፡፡ ‹‹የክርስቶስ ልደት ነዋ፤ በማይክራፎን ሲሰብኩ የሰማሁት እንደዚያ ነው›› ‹‹የት፣ መቼ፣ ለምን ተወለደ?›› ‹‹እነርሱ የሚሉት ቤተልሔም በምትባል ከተማ፣ በእኩለ ሌሊት፣ በብርድ ወቅት፣ ራቁቱን፣ እናቱ በከተማዋ ማደሪያ የሚሰጣት አጥታ፣ በተናቀው ቦታ በከብቶች በረት ውስጥ ተወለደ፡፡ በጣም ስለበረደውና ራቁቱን ስለነበር ከብቶቹ በትንፋሻቸው አሞቁት፤ ሌላ ሰው ስላልነበረ እረኞቹ መጥተው ዘመሩለት፡፡ እንዲህ ነው የሰማሁት፡፡›› ‹‹እኛምኮ እንደርሱ የሚያስጠጋን አጥተን ነው ጎዳና የወደቅነው፡፡ እንደርሱ ራቁታችንን ነን፤ እንደርሱ የሚበላ የለንም፤ እንደርሱ እኛንም የሚያሞቁን እነዚህ ውሾች ናቸው፤ እንደርሱ እኛም በተናቀው ቦታ ላይ ነን›› አለ ሁለተኛው ልጅ ውሻውን እየደባበሰ፡፡ ‹‹የሚገርምህ ነገር ጌታ የተወለደው በከብቶች በረት ዋሻ ውስጥ ነው፡፡ ያኔ ጥድ የለም፤ በረት እንጂ፡፡ ጌታኮ ጫካ ውስጥ አልተወለደም፡፡ ያኔ ከረሜላ የለም፤ ያኔ ጥጥ የለም፣ ያኔ ፖስት ካርድ የለም፣ የሰብአ ሰገል ወርቅ፣ ዕጣንና ከርቤ እንጂ፡፡ አሁን ይኼን ሁለ ከየት እንዳመጡት እንጃ፡፡ ይልቅስ ራቁታችንን ሆነን፣ የሚበላ ናፍቆን፣ በእንግዶች ማረፊያ ሥፍራ የሚሰጠን አጥተን፣ ከእንስሳት ጋር ተኝተን እኛ አለንላቸው፡፡