Friday, August 04, 2017

እንጨት ሽበት

በስቴቶስኮፑ ላይ  ዝናውን ደርቦ፣
ዶክተሩ ብቅ ሲል ስድብን ተርቦ፣
ነጭ ላብ  ሲያመነጭ ተሜ ከግንባሩ፣
ዋርዱም ይጨነቃል ይቆማል ባንድ እግሩ።
አሁን በቀደምለት !
ምሁር ከኔ በላይ አዋቂነት ላሳር፣
ነው ብሎ የሚያምን ከንቱ ነው ስንክሳር፤
ዝም በል አትንጣጣ እንደ ተልባ ቆሎ፣
ስትጠየቅ ብቻ መልስ ስጥ በቶሎ።
በሽታውን ካወቅህ መድኃኒቱን አምጣ፣
የማትችል ከሆነ አማራጭ ምታጣ፣
በመስኮት  ልጣልህ ወይም በበር ውጣ፣
አንች ደግሞ ዝፍዝፍ ምን ተዘርግፈሻል፣
ስታጨሽ ስትቅሚ ቀን ነግቶ ይመሻል፤
ሀገርሽ ወዴት ነው ትመስያለሽ ጭቁን፣
ለካስ ወሎዬ ነሽ የተቋቋምሽ ድርቁን።
አንተን ደግሞ አለት ራስ ተስፋህ የጨለመ፣
አስተምሮ ሰው ሊያረግ ማን ለምን  አለመ?
አድረህ ላትሻሻል በከንቱ ደከመ።
ገዳይ የለም እንጅ ሟችማ መች ጠፋ፣
ድንቁርናም በዛ ባዶነት ተስፋፋ።
እያለ ሲዘልፈን ሲሰድበን ሲቆጣን፣
ቁም ቅምጥ ሲነሳ መድረሻ ሲያሳጣን፤
አባቱን ሊጠይቅ የመጣ አንድ ጎልማሳ፣
እንዲህ ሲል ተቀኘ ብዕሩን አነሳ፣
አወይ እንጨት ሽበት አጉል ሽምግልና፣
ለማንም የማይበጅ ከንቱ ፍልስፍና፣
ጥበብ በፀጋ እንጅ መች በእድሜ ሆነና።

ጌች ቀጭኑ ከ“ward” መልስ ሐምሌ 25/2009 .

No comments:

Post a Comment