Wednesday, June 07, 2017

⛅ሙሉዋ ጨረቃ⛅

ሙሉዋ ጨረቃ
ብሩህ ነሽ ደማቃ
ታለቅሳለች ነብሴ ተስፋ ትቆርጥና፣
በውበትሽ ተማርካ በመራቅሽ አዝና።
ብሆን ከወለሉ አንቺም ጣሪያ ላይ
ዝቅዝቅ ከሚያዩትስ እሚያምር የለም ወይ?
አንገትን ሲያቀኑ ብቻ ነው ማማሩ፣
ያም ይሄም ያም ይሄም ዐይንን ማጭበርበሩ፣
ፈክቶ መታየቱ ሽልምልም ማለቱ
በሩቅ ማጓጓቱ?
ለዓይንም ሌላ  ዓይን አለው
-አንድን ጥርኝ አፈር-
ድንጋይ ብሎ እሚያስጥል በየጉራንጉሩ፤
ወርቅ ብሎ እሚያስቋጥር በየማህደሩ፤
እኔውም  ብሆን ነው የዓይኔ ዐይን ባርያ፣
ሳውቀው መሆንሽን የሌሎች አምሳያ፣
ጉልላት ያረኩሽ የፍጥረት እናት፣
በውን እምትሞቂ ድንቅ የሕልም እሳት።
ዳኛ ነው የሚፈርድ ምክንያት ጠቅሶ መጽሐፍ አንብቦ
ግን ከሳሽ ተከሳሽ/ያው እንደኔ እንዳንቺው/
ስሜቱን አንግቦ
አእምሮው ረግቦ
አውቃለሁ እንዳይሻር ይህ ብሉይ አዋጅ፣
ከአለኝታዬ አይጃጅ በምኞቴ አይዋጅ፣
እንደነበር ሲኖር መታከት መታከት
መታከት ነው እንጅ።
ነውናም ስገብር ለዐዋጁ ለዕጣዬ፣
አንቺ ዝቅ ብለሽ ወይ እኔ ከፍ ብዬ፣
እንገናኝ ይሆን? ሆኗል ጥያቄዬ።

ምንጭ ፦ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ
            በደበበ ሰይፉ

No comments:

Post a Comment