Thursday, April 27, 2017

ዜና እረፍት

እማሆት ትሻሌ በሰፈራችን በጣም የተከበሩ መነኩሲት ነበሩ።እረፍት ላይ እያለሁ በፀና መታመማቸውን ሰማሁና ለመጠየቅ ከአባዬ ጋር ጎራ ብዬ ነበር።ወደ ትንሿ ቆርቆሮ ቤታቸው ስንገባ የሰኞው መደብ ላይ ካለው በዝንቦች ተወሮ ንብ የሰፈረበት የሚመስል ጎጃም አዘነ በቀር ማንም አልነበረም። አባዬ ደና አደርሽ እሟሐይ ሲል በዝንብ ከተወረረው አዘነ ውስጥ እግዚሀር...ይመስገን የሚል ድምፅ ተሰማ። እኔም አከታትዬ እንደምን አለሽ እማማ? አልሁ ድምፁ ከዚያ አዘነ ውስጥ መውጣቱን እየተጥራጠርኩ። አሁንም እ..ግ..ዚ..ሀ..ር ይመስገን አሉ መነኩሲቷ ልብሱን ከፊታቸው ለማንሳት እየሞከሩ። ደጋግፈን አነሳናቸውና ተቀመጡ። ያቃስታሉ፤ ሰው ማለዬት አይችሉም፤ እግራቸው  እስከ ጉልበታቸው ድረስ አብጧል፤ ሰውነታቸው ይንቀጠቀጣል። “.........እንዴው እንዴት እንዴት ነው ይሆን  ሚያደርግሽ?”“...እህ... እህ.... ውጋት እህ.... እህ... ጎኔን ይወጋኛል..... እራሴን ይወግረኛል... ዓይኔን ይደነግረኛል... የሰራ አከላቴን ይሸቀሽቀኛል... እህ...ወጥቼ መግባት አልችል... ይኸው የአልጋ ቁራኛ አድርጎኝ ተቀመጠ እንጂ እህ....እህ... እህ....።” ...............................ከትቂት ጭውውትና ከብዙ ትካዜ በኋላ “እና በሀኪም መታየቱ ይሻላል እኮ ሆስፒታል እንውሰድሽ እንጅ” የሚል ጥያቄ አቀረብኩ። እማሆይ በሚቆራረጠው ድምፃቸው “ሀኪምስ ክ..ክርስቶስ ነው፤እህ... እህ... እርሱ ያመጣውን መቻል ነው እንጅ እህ... ምን ብዬ ነው ሆስፒታል ምኸድ?”አሉ። መነኩሲቷ ወደህክምና እንዲሄዱ ለማግባባት ሞከርኩ እርሳቸው ግን ከአሁን በፊት ምንም አይነት የሀኪም መድኃኒት ወስደው እንደማያውቁ ፤አሁንም ከአቋማቸው ንቅንቅ እንደማይሉ በመግለፅ እንቢ አሉ።...........ይህ በሆነ በ12ኛው ቀን ሚያዝያ 11/2009ዓ.ም ማረፋቸውን በስልክ ሰማሁ። እርሳቸው አረፉ ቃላቸው ግን አሁንም ያስተጋባል። “ሀኪምስ ክ..ክርስቶስ ነው” እያለ። እማሆይ ትሻሌ አይቸው በህይወት ዘመናቸው ሁሉ በጣም የተመሰገኑ በወጣትነታቸውም መልከ መልካም ለጋስ ሩህሩህና መነፈሰ ጠንካራ ሴት እንደነበሩ የሚያውቋቸው ይናገራሉ።
“የጠገበው ሲሄድ የራበው ሲመጣ፣ 
ወይዘሮ ትሻሌ ምጣድሽ አይውጣ።” ተብሎም ተዘፍኖላቸዋል።የሚያስደነገጥ ወይም የሚያስፈራ ነገር ሲያጋጥማቸው በመጮህ ፋንታ  “ዘራፍ ትሻሌ አይቸው!” ማለት ይቀናቸው እንደነበርም የብዙዎች ትዝታ ነው። ሞት አሸነፋቸው እንጅ። እንግዚአብሔር ነፍሳቸውን በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ አጠገብ ያኑር። አሜን!

No comments:

Post a Comment