Wednesday, September 04, 2024

በልብስ ወበሢሳይ ኢታርእዪኒ ንዴተ

 በልብስ ወበሢሳይ ኢታርእዪኒ ንዴተ

እስመ ቁር ወረኃብ ያረስእ ጥበባተ
በአፄ ምኒልክ ዘመን አለቃ ተክሌ የሚባል የንጉሥ ተክለኃይማኖት አሽከር በአፈ ንጉሥ ይግዛው ስም የተንኮል ማህተም ቀርጠኻል በሚል ተወንጅሎ እስር ይፈረድበታል። ወህኒ ቤት በገባ ጊዜም "ስለ እግዚአብሔር ብለው አይርሱኝ፤ ለጃንሆይ ያስተዛዝኑልኝ፤ ዘመድ የለኝም"ብሎ አሳላፊ ውቤን ወደ እጨጌ ወልጊዮርጊስ ላከ። አለቃ ተክሌ ወህኒ ቤት ሳለ መልክአ ኤዶም ይደግም ነበረ። ያን ጊዜም ከበጅሮንድ ገድሌ ቤት ታሥሮ የተቀመጠው አለቃ ተገኝ "ወረድኦ ለነዳይ በተጽናሰ (ችግረኛውን በችግሩ ጊዜ ረዳው)" የሚል ሕልም ስለ አለቃ ተክሌ አየ።
አለቃ ተክሌ መልክአ ኤዶም እየደገመ ባዘነበት የሰኔ ማርያም እለት እጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ ለእቴጌ ጣይቱ ነገረለት። እቴጌ ጣይቱም "ለጃንሆይ ነግሬ አስፈታዋለሁ፤ ጉራምባ ማርያምን ይሥልልኛል" አለች። ከዚያም " አለቃ ተክሌን ፈተው ለእኔ ይስጡኝ፤ ጉራምባን ይሣልልኝ፤ በሎልነቱ ታዝዞ ማኅተም ቢሰራ በርሱ ምን ኃጢአት አለበት ?" አለችና ለጃንሆይ ተናገረች። እጨጌ ወልደጊዮርጊስም አከታትሎ አስተዛዘነለት ።አፄ ምኒልክም "እሽ ይፈታ" አለ።
ለአማኑኤል ተስሎ ቀሚሱን በሰጠበት ሰኔ ፳፰ ቀን የአማኑኤል ዕለት ከወህኒ ቤት ወጣ። ከተፈታ በኋላ ለእቴጌ ሹም ለአዛዥ
ዘአማኑኤል ተላለፈ። አዛዥ ዘአማኑኤልም ራት ምሣውን፣ ምንጣፍ ሥፍራውን አዘዘለትና በማዕረግ ተቀመጠ። ነሐሴ ፪ ቀን እቴጌ ጣይቱ ሙያውን ልትሰልል "ሥዕለ ማርያም በወረቀት ሥለህ ስደድልኝ" ብላ ላከችበት። እርሱም ፩ ሉክ ወረቀት ተቀብሎ ጥሩ ሥዕል ሥሎ ከሥዕሉ ግርጌ
ኢትኀድግኒ ዓቂበ
በልብስ ወበሢሳይ ኢታርእዪኒ ንዴተ
እስመ ቁር ወረኃብ ያረስእ ጥበባተ
[መጠበቅን አትተይኝ
በልብስና በምግብ ችግር አታሳይኝ። ብርድና ረሃብ ጥበብን ያስረሳልና።] የሚል ጽሑፍ ጽፎ ሰደደላት።
እቴጌ ጣይቱም ሥዕሉን አይታ አደነቀች ፤ለጃንሆይም አሳየች ። ከሥዕሉ ግርጌ ያለውን ጽሑፍ ባየች ጊዜ አዛዥ ዘአማኑኤልን ተቆጣች። "ካላስራብኸው እንዲህ ብሎ አይልክም" አለች። አዛዥ ዘአማኑኤልም ከመጣ እስከ ዛሬ ድርጎው አልገደለበትም። "እንዲያው ጎጃሞች ልፍ(ማሳጣት፣ክስ) ይወዳሉ "አለና አለቃ ተክሌን ተጣላው። እቴጌ ጣይቱ ግን የሰርክ ልብስ፣የሌሊት ቡልኮ፣ ለቀን ጥበብ ኩታ፣ እጀ ጠባብና ሱሪ በርኖስ ዳረገችው። ነሐሴ ሲያልቅ ጳጉሜ ፫ ቀን ጉራምባን ይሣል ብላ ፫ ዳውላ እህል ቀለብ፣ ፪ ጉንዶ ማር፣ ለወር ፩ ሙክት፣ ለ ፲ ቀን ፭ ኩባያ አሻቦ፣ ፩ እቃ ቅቤ፣ ጾም ቢሆን ቅባኑግ ለወር ዳረገችው። የቀለም መበጥበጫ ፲፪ ፍንጃል አዘዘች።
ኢትኀድጉኒ ዓቂበ
በልብስ ወበሢሳይ ኢታርእዩኒ ንዴተ
እስመ ቁር ወረኃብ ያረስእ ጥበባተ
[መጠበቅን አትተውኝ
በልብስና በምግብ ችግር አታሳዩኝ። ብርድና ረሃብ ጥበብን ያስረሳልና።]


No comments:

Post a Comment