Wednesday, September 04, 2024

ኑ! ሆስፒታሉን ሆስፒታል እናስመስል

ግርማዊነታቸው ከጣሊያን ጦርነት በኋላ ከስደት ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የጎጃም እምብርት ላይ በምትገኝና ወጀት ተብላ በምትጠራ ትንሽዬ ከተማ ላይ ከአጃቢዎቻቸው ጋር እረፍት ያደርጋሉ። እስከዚያን ጊዜ ድረስ ያደረጉት ጉዞ በሰላም የተሞላ ነበርና ከተማዋን ፍኖተ ሰላም ብለው ሰየሟት። የሰላም መንገድ ማለታቸው ነው፡፡ ከከተማዋ ወጣ ብለውም ለማስታወሻ ይሆን ዘንድ አንድ ዋርካ ተከሉ።

ጃንሆይ በቆይታቸው ሰው ሰው አክባሪ፤ወዲህ እንግዳ ተቀባይ፤ አካባቢው ጤፍ፣ በቆሎ፣ ዳጉሳ፣ ኑግ፣ በርበሬ እና ሌሎችንም የእህል አይነቶች የሚያበቅል፤ ሎሚ፣ ብርቱካንና ፓፓዬ እንደልብ የሚግኝበት፤ በተፈጥሮ ለምነትን የታደለ፤ መሆኑን አስተዋሉ። የባከልን ቡና ቀምሰውም በጣዕሙ ተደመሙ። ጃንሆይ ምልከታቸው በዚህ አላበቃም፡፡ የአካባቢው ህዝብ በስጋ ደዌና በቲቪ በሽታ እንደሚሰቃይ አይተው አውጥተውና አውርደው ሆስፒታል አስገነቡለት፡፡
ከ62 ዓመታት በፊት ቲቢና ስጋ ደዌ በሽታን ለማከም ታስቦና አብዛኛው ወጪው በህዝቡ ተሸፍኖ የተገነባው ፍ/ሠላም ሆስፒታል በ1976 ዓ.ም በከፍተኛ የአካባቢዉ ማህበረሰብ ተሳትፎ ማስፋፊያ ተደርጎለት በገጠር ሆስፒታል ደረጃ ለማደግ የቻለ ሲሆን፤ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ጠቅላላ ሆስፒታልነት በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ለማደግ ችሏል፡፡ ተቋሙ 297 የጤና ባለሟያዎች እና 102 የአስተዳደር ሰራተኞች በድምሩ 399 ቋሚ ተቀጣሪ ሰራተኞችን ይዞ ለአካባቢው ማህብረሰብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይግኛል፡፡
በ2016 ዓ.ም 88,230 የተመላላሽ ታካሚዎችን ፣5,704 ተኝቶ ታካሚዎችን ፣ 11,462 የድንገተኛ ክፍል ታካሚዎችን፣3,479 የወሊድ አገልግሎት፣1,754 ከፍተኛ ቀዶ ጥገና ስራዎችን እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የሆስፒታል አገልግሎቶችን ሲሰጥ የከረመ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በቀን 400-600 ህሙማንን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ሆስፒታሉ በስሩ አምስት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ማለትም( ፈረስ ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ደምበጫ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ፣ቡሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ፣ዱርቤቴ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ፣ሊበን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል) እንዲሁም ሶስት የከተማ ጤና ጣቢያዎችን( ቋሪት ጤና አጠባበቅ ጣቢያ፣ ጅጋ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ፣ፍ/ ሰላም ጤና አጠባበቅ ጣቢያ) በስሩ በክላትተር ትስስር ይዞ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጅ ይህ የእድሜ ባለጸጋ ሆስፒታል ከአቻዎቹ ጋር እኩል ማደግና ዘመኑን የዋጀ እንዲሁም ያለውን የታካሚ ፍሰት የሚመጥን አገልግሎት መስጠት ባለመቻሉ በተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይነሱበታል። በቅርቡ ባዲስ መልክ የተዋቀረው የሆስፒታሉ ማኔጅመንት ይህንን ችግር ለመፍታት ኮሚቴ አቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ኮሚቴውም ሆስፒታሉ የሚጠበቅበትን አገልግሎት በአግባቡ እንዳይሰጥ ማነቆ የሆኑበትን ችግሮች በመለዬት እንደ ችግሩ ስፋትና ክፋት በቅደም ተከተል ለመፍታት ደፋ ቀና በማለት ላይ ነው፡፡
ስለሆነም የፍኖተሰላም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች፣ተወልጆች፣ባልሃብቶች፣አዋቂና ታዋቂ ሰዎች፣የሚመለከታችሁ የመንግስት አካላት፣መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆናችሁ ድርጅቶች ሆስፒታሉን ሆስፒታል ለማስምሰል በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ተቋሙን እንደ ራሳችሁ ቤት ቆጥራችሁ ከጎናችን እንድትቆሙ ስንል በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡
ለዚሁ ዓላማ ብቻ የተከፈተውን የtelegram group ይቀላቀሉ


No comments:

Post a Comment