የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የወላዲተ አምላክ የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ሁላችሁም እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ። ልዑል እግዚአብሔር ፈጣሪያችን የባሕርይ አምላክ ሲሆን በፍጥረቱ የማይጨክን ርኅሩኅ ነውና ሊያድነን ስለፈቀደ ፍጹም ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዷልና ዛሬ የልደቱን በዓል ለምናከብርባት ዕለት እንኳን አደረሳችሁ። ሱባኤ ከተቆጠረ፣ትንቢት ከተነገረ በኋላ ማለትም ቅዱሳን ነቢያት ይመጣል፣ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ብለው ተናግረው ከጨረሱ በኋላ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን አምላክ ከአንቺ ይወለዳል ብሎ አበሰራትና ጊዜው ሲደርስ ማለትም 5500 ዘመን ሲፈጸም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተልሔም በተባለው ቦታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ።ኲነኔ፣ፍዳ፣መርገም፣ኀዘንና ኃጢአት ሁሉ ተደመሰሰ ። አንድነት ፣ ስምምነት፣ርኅራኄ፣ሰላምና ፍቅር ሰፈነ። ስለዚህም ዛሬ የምናከብረው ይህንን ታላቅ ዕለት የጌታችንን ልደት ነው። ልደት፦ትርጉሙ ከማኅጸን መወለድ ፣ከእናት ሆድ ወደ ብርሃን መውጣት፣መገኘት፣ተገልጾ መታየት ማለት ነው።
በአንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ “ፈጽሞ ሰው ሆነ” ሲባል በመጀመሪያ በጽንሰቱ በኋላም በልደቱ አምላክ ወልደ አምላክ በሥጋ መገለጡን ያመለክታል። በድንግል ማኅጸን ሳለ ጥቂት ቅዱሳን ብቻ ያውቁት ነበር፤ ከልደቱ በኋላ ግን ለዓለም ሁሉ ተገለጠ። ሕዝብም አሕዛብም የሚያዩት የሚዳስሱት ሰውነት ያለው ሆኖ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ እንደ ሰው ተገልጧል ። የአሁን አመጣጡ በስጋ በመገለጥ ነው፤ የቀድሞው አመጣጡ ግን በመለኮታዊ እሳት አምሳል ስለነበር ማንም ሊቀርበው አይችልም ነበር። ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መገለጥ በሚታይ በነበልባል ውስጥ ነበር። በእሾህ ቁጥቋጦ መካከል በሚነደው እሳት የተገለጠው አምላክ ለሙሴ ብቻ ነበር። ወደ ተቀደሰውም ቦታ ጫማውን አውልቆ እንዲቀርብ ለሙሴ ተነግሮት፣እርሱም በፍርሃትና በመደነቅ ለምለሙ ቁጥቋጦና ነበልባሉ ተዋሕደው ወደሚታዩበት ኅብረ ትርእይት ተጠግቶ የአምላክን መገለጥ አይቶ የዘላለም ስሙም “ ያለና የሚኖር” እርሱ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እንደሆነ ለማወቅ በቅቷል ዘጻ 3፥1-15 ይህ የብሉይ ኪዳን መገለጥ ነበር።
በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የታየው የአምላክ መገለጥ በሥጋ ነበር። ይህም ሥጋ ከእመቤታችን ተገኝቷል ። ስለዚህ እመቤታችን እንደ ለምለሙ ቁጥቋጦ ትመሰላለች፤የእሳቱ ነበልባልም በማኅጸኗ ያደረው መለኮት ነው ማለት ነው። ነበልባሉ ለምለሙን ቅጠል እንዳላቃጠለው፣እንደዚሁም በእመቤታችን ያደረው እሳተ መለኮት ሥጋዋን እንዳላቃጠለው ከምሳሌው እንረዳለን። እግዚአብሔር በሥጋ የተገለጠባትን የሐዲስ ኪዳኗን ቁጥቋጦ ለማየት የሚጠጋ ሁሉ ጫማውን አውልቆ በአክብሮት ይመለከታታል። ይህንን ለማየት እድል የተሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ ቅድስት ኤልሳቤጥና ቅዱስ ዮሴፍ ነበሩ። የእመቤታችንን ድምጽ ስትሰማ የኤልሳቤጥ ጽንስ ከማኅጸኗ ሆኖ በደስታ ዘለለ፤በአክብሮት ሰገደ። ይህ ታላቅ ተዓምር ነው። ስለዚህ ነው ዘመዷ ኤልሳቤጥ “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” በማለት በታላቅ ድምጽ ጮሃ የተናገረችው ሉቃ 1፥39 ስለዚህ ነው ቅዱስ ዮሴፍም በፍርሃትና በአክብሮት እመቤታችንን የሚጠብቃትና የሚያገለግላት።
በኦሪት ታላቁ መገለጥ በሲና ተራራ ነበር። ያን ጊዜ ቃለ አብ ሕያው በተራራው ላይ ወርዶ በሚነደውና በሚያስፈራው እሳት መካከል ሲገለጥ የነጎድጓዱና የመለከቱ ድምጽ፣የመሬቱ መናወጥ የጭጋጉና የጨለማው ሁኔታ በተራራው ስር ለነበሩት የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ሲታይ እጅግ የሚያስደነግጥ እንደ ነበር ተጽፏል ዘጻ 19፥16 ። በወንጌል የታየው መገለጥ ግን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ሳይሆን ፣በአርኅቶ ርእስ፣በአርአያ ግብርና የጌታ ሰው መሆን ነበር። እርሱም በሲና ተራራ ላይ የወረደ፣ ከእመቤታችን በሥጋ የተወለደ የአብ ሕያው ቃል ነበር። ስለዚህ ነው እመቤታችን “ደብር ነባቢት በትኅትና” የተባለችው ይህም ማለት በትህትና የምትገኝ ፣ የምትናገር እግዚአብሔር የተገለጠባት የተቀደሰች ተራራ እመቤታችን መሆኗን የሚያመለክት ነው። ከኦሪት መገለጥ በወንጌል በሥጋ የተገለጠው ይበልጣል ። የሰው ልጆች የመዳን ተስፋ የተፈጸመው በጌታችን ልደት ነውና ።ስለዚህ የጌታን የልደቱን ታሪክ ስንማር የእግዚአብሔርን ፍቅርና ውለታ እያሰብን እርሱን ከማመስገን ጋር ይሁን።ታሪኩም እንደሚከተለው ነው፦
“በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽህፈት ሆነ ።ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ሔደ፣ ጸንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤የበኲር ልጅዋንም ወለደች። በመጠቅለያም ጠቀለለችው ለእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ ። እነሆም የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፤ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው ፦ እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፣ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፣ ሕጻን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ።እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ” ሉቃ 2፥1-14 ።
ከጌታ የልደት ታሪክ ጋር በተያያዘ ሦስት ታላላቅ ትምህርቶችን እንመለከታለን
1ኛ ጌታ በበረት ስለ መወለዱ
በመጀመሪያ ጌታችን በበረት ውስጥ ስለ መወለዱ እንመለከታለን። የጌታችን ቀዳማዊ ምጽአቱ ማለት የመጀመሪያ አመጣጡ፣በሥጋ መገለጡ ፣ ከበረት ውስጥ መወለዱ እንዴት የሚያስደንቅ ነገር ነው!ከአንድ ድሀ ቤት እንኳ ቦታ ጠፍቶ እንዴት ከከብቶች ማጎሪያ ከበረት ውስጥ ተወለደ!ለወፎች ጎጆ ለቀበሮችም ጉድጓድ አላቸው ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ስፍራ የለውም የተባለውን ያስታውሰናል ፤ ማቴ8፥20 ። እርሱ የጌቶች ጌታ ሲሆን በዝቅተኛ ስፍራ በመገኘት የድሆች ድሀ በመሆን እንደ ትንሽ ሕጻን መልክ በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ተጥሎ የተገኘበት ምክንያት ከቶ ምን ይሆን? መልሱም እንደሚከተለው ነው ። የወደቀውንና የተዋረደውን የጠፋውን አዳምን በመፈለግ እርሱን መስሎ፣ እርሱን አህሎ የፍጡርን ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ዓለም የመጣው እርሱንና ልጆቹን ለማዳን ነው። ከገነት በመውጣቱ በልቡ ያዘነውንና የተከዘውን አዳምን ወደ ቀደመው ክብሩ ጌታ ሊመልሰው ስለወደደ የእርሱንና የልጆቹን ውርደትና ኃጢያት ተሸክሞ ሊያድናቸው ከሰማያተ ሰማያት ወረደ፣ከበረትም ውስጥ ተወለደ።
የሰው ልጆችን ልቦና ለመንካት በእንዴት ያለ ትኅትና በዝቅተኛ ሁኔታ እንደ ተወለደ ተመልከቱ። ይህንንም ያደረገበት ምክንያቱ የወደቀውን የሰው ልቦና ለማደስና ለማንሣት ነው። አዲስ ልቦናን ሊፈጥርልን ትንሣኤ ልቦናን ሊሰጠን ፈልጎ በሥጋ ተገለጠ። እኛ የእርሱን መንፈስ ለመቀበል እንድንችል እርሱ የእኛን ሥጋ ወሰደ ።የእርሱን ልዕልና እንድንወርስ ህይወትም እንድናገኝ እርሱ የእኛን ውርደትና ሞት በሥጋው ተሸከመ። እንደዚህም በማድረጉ ሁላችንንም አዲስ ፍጥረት አደረገን። ስለዚህ ነው በማዳን ሥራው ሁላችንን እንደገና ሊፈጥረን አስቦ ጌታ ሥራውን ሁሉ ከመጀመሩ በፊት ጥበብን ፈጠረ ተብሎ የተነገረው ምሳ 8፥22 ፣ይህም ማለት በሥጋ መወለዱን ለማብሠር ነው።
2ኛ የጌታ ልደት ለእረኞች ስለ መገለጡ
ጸጥ ባለው ሌሊት በሜዳ ላይ ለሚገኙ እረኞች ጨለማውን አርቆ ከሰማይ የወረደላቸው ብርሃን የጌታን ክብርና ልዕልና የሚያስረዳ ሲሆን፣ የጌታ መልአክም ተገልጾ ነብይና ሐዋርያ በመሆን ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆነውን ታላቅ ደስታ አብስሯቸዋል። ለእነርሱ መዳን ሲል የመጣውን ጌታ ክርስቶስ በዳዊት ከተማ መወለዱን ነገራቸው። ሄደውም ለማየት እንዲችሉ “ሕጻኑ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ላይ ተኝቶ ታገኙታላችሁ” በማለት ምልክቱን አስታወቃቸው። የጌታን ልዕልናና ትኅትና በአንድ ጊዜ ለማየት የሚችሉ በድንገት ብዙ ሠራዊተ መላእክት ተገልጠው፣ ጌታን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በመንበሩ ላይ ሆኖ በሰማያት ስላዩት “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም /በሰማያት/ ይሁን” አሉ፤ ደግሞም ከታች በትኅትና በምድር ላይ ሆኖ በግርግም ላይ ተኝቶ በማየታቸው “ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” በማለት ለጌታ ልደት የሚገባ ምስጋናና መዝሙር አቅርበዋል ።
እረኞችም ይህንን ሁሉ ታላቅ ታምራት አይተው ዝም አላሉም ። በተሰጣቸው ምልክት መሰረት ወደ ቤተልሔም ፈጥነው በመሄድ እንደተጻፈው ”ማርያምንና ዮሴፍን ሕጻኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ።አይተውም ስለዚህ ሕጻን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። እረኞችም እንደተባለላቸው ስለሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ /ሉቃ 2፥16/ እነርሱም በጌታ መልአክ የተሰበኩ የመጀመሪያወቹ አማኞች ነበሩ። ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ ለሰዎች በመንገራቸው ለጌታ ልደት ምስክሮች ሆነዋል ። እኛም ለሰዎች መዳን ይህን ታላቅ ተዓምር ያደረገውን በሥጋና በደም የተገለጠውን ጌታ ከቤተልሔም ማለት ከቤተ ክርስቲያን ሔደን እንፈልገው፣ሥጋውንና ደሙን በመቀበል እንወቀው፣እንመነውም እናክብረውም “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” በማለት ሁል ጊዜ በጸሎተ ቅዳሴ እናመስግነው።
3ኛ ሰብአ ሰገል
ጌታ በተወለደ ጊዜ በምድር ብቻ ሳይሆን፣በሰማይም ላይ አዲስ ተዓምር ታየ ። ለዓለሙ ሁሉ የሚታይ አዲስ ኮከብ ተወለደ። የጌታ መልአክ ለእረኞቹ ስለጌታ ልደት እንደነገራቸው፣ እንደዚሁም ኮከብ በመታየቱ ብቻ ለአሕዛብ ሁሉ ልደቱን አበሰረ። በኮከቡም እየተመሩ ሰብአ ሰገል የተባሉ የምስራቅ ጠቢባን /ነገሥታት/ ኢየሩሳሌም ደረሱ። የአይሁድ ንጉሥ የት እንደተወለደ በመጠየቃቸው በዘመኑ የነበረው ንጉሥ ሄሮድስና የኢየሩሳሌም ከተማ ሁሉ በሰሙት አዲስ ዜና ተደናገጡ። በትንቢት እንደተነገረው ከቤተልሔም እንደሚወለድ ስለተረዱ ሰብአ ሰገል ከቤተልሔም ከተማ ገቡ። ያዩትም ኮከብ ሕጻኑ እስከሚገኝበት ቦታ ድረስ መራቸው። “ወደ ቤትም ገብተው ሕጻኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት ፣ ወድቀውም ሰገዱለት፣ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፣ዕጣንና ከርቤም አቀረቡለት” /ማቴ 2፥11/። የስጦታዎቹም ትርጉም ወርቅ የጌታችንን ንጉሥነት፣ ዕጣን ክህነቱን፣ከርቤ ክቡር ሞቱን የሚያስታውቀን መሆኑን የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ያስተምሩናል።
እንግዲህ ክርስቲያኖች ጌታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በመስቀል ተሰቅሎ ነጻ አወጥቶናልና ከእንግዲህ በኋላ የሰይጣን ባሮች የዲያብሎስ ተገዥወች መሆን የለብንም ።ስለሆነም በ/1ኛዮሐ 4፥7_ /እንደተነገረን በእውነተኛው ፍቅር አንድ ሆነን ትእዛዛቱን እየፈጸምን እንኑር ። ከበደላችን ሁሉ እንመለስ፣ንስሐም እንግባ ፣ካለንበት ጊዜያዊ ስፍራ በሞት የምንጠራበትን ሰዓት አናውቅምና ስለዚህ ኃጢያታችንን እየተናዘዝን ከኃጢያት ተግባር ንጹሐን ሆነን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እየተቀበልን ለመንግሥተ ሰማያት ልንዘጋጅ ይገባል። ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓሉን የሰላም፣የአንድነት፣የፍቅርና የፍጹም ደስታ በዓል ያድርግልን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ግቢጉባኤ ትምህርት ክፍል ትምህርታዊ ጽሁፍ ዝግጅት ንዑስ ክፍል
No comments:
Post a Comment