የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ የወላዲተ አምላክ የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ሁላችሁም እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ። ልዑል እግዚአብሔር ፈጣሪያችን የባሕርይ አምላክ ሲሆን በፍጥረቱ የማይጨክን ርኅሩኅ ነውና ሊያድነን ስለፈቀደ ፍጹም ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዷልና ዛሬ የልደቱን በዓል ለምናከብርባት ዕለት እንኳን አደረሳችሁ። ሱባኤ ከተቆጠረ፣ትንቢት ከተነገረ በኋላ ማለትም ቅዱሳን ነቢያት ይመጣል፣ከቅድስት ድንግል ማርያም ይወለዳል ብለው ተናግረው ከጨረሱ በኋላ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቅድስት ድንግል ማርያምን አምላክ ከአንቺ ይወለዳል ብሎ አበሰራትና ጊዜው ሲደርስ ማለትም 5500 ዘመን ሲፈጸም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተልሔም በተባለው ቦታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ።ኲነኔ፣ፍዳ፣መርገም፣ኀዘንና ኃጢአት ሁሉ ተደመሰሰ ። አንድነት ፣ ስምምነት፣ርኅራኄ፣ሰላምና ፍቅር ሰፈነ። ስለዚህም ዛሬ የምናከብረው ይህንን ታላቅ ዕለት የጌታችንን ልደት ነው። ልደት፦ትርጉሙ ከማኅጸን መወለድ ፣ከእናት ሆድ ወደ ብርሃን መውጣት፣መገኘት፣ተገልጾ መታየት ማለት ነው።
በአንቀጸ ሃይማኖት ውስጥ “ፈጽሞ ሰው ሆነ” ሲባል በመጀመሪያ በጽንሰቱ በኋላም በልደቱ አምላክ ወልደ አምላክ በሥጋ መገለጡን ያመለክታል። በድንግል ማኅጸን ሳለ ጥቂት ቅዱሳን ብቻ ያውቁት ነበር፤ ከልደቱ በኋላ ግን ለዓለም ሁሉ ተገለጠ። ሕዝብም አሕዛብም የሚያዩት የሚዳስሱት ሰውነት ያለው ሆኖ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ እንደ ሰው ተገልጧል ። የአሁን አመጣጡ በስጋ በመገለጥ ነው፤ የቀድሞው አመጣጡ ግን በመለኮታዊ እሳት አምሳል ስለነበር ማንም ሊቀርበው አይችልም ነበር። ያን ጊዜ የእግዚአብሔር መገለጥ በሚታይ በነበልባል ውስጥ ነበር። በእሾህ ቁጥቋጦ መካከል በሚነደው እሳት የተገለጠው አምላክ ለሙሴ ብቻ ነበር። ወደ ተቀደሰውም ቦታ ጫማውን አውልቆ እንዲቀርብ ለሙሴ ተነግሮት፣እርሱም በፍርሃትና በመደነቅ ለምለሙ ቁጥቋጦና ነበልባሉ ተዋሕደው ወደሚታዩበት ኅብረ ትርእይት ተጠግቶ የአምላክን መገለጥ አይቶ የዘላለም ስሙም “ ያለና የሚኖር” እርሱ የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እንደሆነ ለማወቅ በቅቷል ዘጻ 3፥1-15 ይህ የብሉይ ኪዳን መገለጥ ነበር።