Thursday, December 03, 2015

የግቢ ማስታወሻ

ሰላምይሁን ተውልዶ ያደገው በባህር ዳር ከተማ  ሲሆን የህይወት አስቸጋሪ ውጣ ውረዶችን የጀመረው ገና በሕጻንነት እድሜው እንደሆነ የሚያውቁት ይናገራሉ። ከዕለታት አንድ ቀን መሐል ፒያሳ ላይ ቆሟል። ምን ማድረግ እንዳለበትም ሆነ የት መሄድ እንዳለበት በትክክል ። መለየት ተስኖታል። በዚያ ላይ ረሀብ በጣም እያስቸገረው ነው። ሲያስበው ትናንትና ጥዋት ላይ ምግብ ወድ አፉ መጠጋቱ  ትዝ አለው። ያለው ብቸኛ አማራጭ ሁሌም ሰዎች ሲያደርጉት የሚያናድደውን ተግባር እርሱም መፈጸም እንደሆነ አመነበት። እናም ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ መብራት ኃይል ሕንፃ በሚወስደው የግራ መስመር ላይ ቆሞ ታክሲ ለመሳፈር ከሚጋፉት ሰዎች አጠገብ ደረሰ። ልቡ በአፉ በኩል ወጥታ ለመሄድ የምትታገለው እስኪመስለው ድረስ ፍርሃት እየናጠው ታክሲ ጥበቃ አጠገቡ የቆመውን ሰው ማናገር ጀመረ። ግን ገና ፊቱ ለመለመን መዘጋጀቱን በሚያሳይ ሁኔታ ሲቅለሰለስበት "እግዚአብሔር ይስጥህ" ብሎት ቦታ ቀየረ። አሁን ሰላምይሁን አይኖቹ እንባ አቀረሩበት በዚህ መንገድ መለመን ከቀጠለ ማንም ምላሽ እንደማይሰጠው ወዲያውኑ ተገነዘበ። እንደ ምንም ብሎ ወደ ኋላ በማፈግፈግ አንድ ጥግ ላይ ተቀምጦ ቀጥሎ ማድረግ ያለበትን ነገር ማውጠንጠን ተያያዘ።


ጭንቅላቱ መፍትሄን ከመፈለግ ይልቅ "ለምን ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ሆነ?" የሚለው ጥያቄ ፋታ ሊሰጠው አልቻለም። ወደ ላይ እና ወደታች የሚራወጡትን የአዲስ አበባ መኪናወች፣የሰዎችን ሩጫና የተደበላለቀውን ጩኸት ሲያስተውል በእርሱ ውስጥ ያሉ የሃሳብ ብዛት በአካል የታዩ መስሎት ፈገግ ማለት አሰኘው። በፊት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመከራ ጨርሶ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ሁሉም ነገር ይስተካከላል በማለት ሲመካ የነበረው ነገር ጭራሽ ሁሉም ነገር ተዘበራርቆ ለእርሱ ዩኒቨርሲቲ የምድር ሁሉ መከራ መለማመጃ መሆኑ ሁሌም ይገርመዋል። የሚወዳቸው እናቱ በአስጊ ሁኔታ የኩላሊት በሽተኛ ስለሆኑ ምን ማድረግ እንዳለበት ተስኖታል። እርሱ የጀመረውን የኢንጂነሪንግ ትምህርት ጨርሶ ለመውጣና እናቱን ለመጦር ከሚያልመው የበለጠ ሌላ ተስፋ በህይዎቱ ውስጥ አለኝ ብሎ አስቦ አያውቅም ነበር። አባቱ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ምክንያት ለስራ በወጡበት ሳይመለሱ በመቅረታቸው ገና ክርስትና ከተነሳበት ሳምንት ጀምሮ እናቱ በመከራ ነው ያሳደጉት። እናቱ ወ/ሮ ብርሃን ለእርሱ በትክክል የሕይወቱ ብርሃን መሆናቸውን ያምናል፤እርሳቸው ከሌሉ አበቃ! ብርሃኑም ይጠፋል። ይህ ነው የሰላምይሁን ጭንቀት።


የአምሮው ጓዳ ደግሞና ደጋግሞ ዐስሩ ቦታ ሲረግጥበት፣ወደኋላ ተመልሶ የትዝታ ዓለም ውስጥ ገብቶ መዋኘት ነው የሚያምሬው። እናም አሁንም መንገድ ዳር መቀመጡን እንኳ ሳያስተውለው የኋላ ማርሽ አስገብቶ ትናንትና ላይ ደርሷል። ወ/ሮ ብርሃን ነፍስ ካወቀብት ጊዜ ጀምሮ በእናትነታቸው ሲያስታውሳቸው እርሱን ለማሳደግና ከፍቶት እንዳይውል ለማድረግ የማይሆኑት ነገር አልነበረም። ምንም ያክል ሕይወት ቢከፋም የዕለት ጉርስ ለማግኘት ይህን ሁሉ ዘመን አንድ ጊዜ እንጀራ ሲሸጡ ሌላ ጊዜ ሰው ቤት በተመላላሽ ሰራተኝነት ሲሰሩ፣አንዳንዴም  ድግስ ቤቶች እየተጠሩ ወጥ በመስራት ብዙ መከራ ተቀብለዋል። ሰላምይሁን 8ኛ ክፍል ከደረሰ በኋላ ግን የሚወደውን ትምህርት ሳያቋርጥ ተወልዶ ባደገበት የባሕርዳር ከተማ ውስጥ ባሉ የንግድ ሱቆች የመላላክ ስራ ጀመረ፤በኋላም የሰፈሩ ልጆች ያላቸውን ሳይክሎች በማከራየት እናቱን መደጎም ቻለ። በኋላ ዩኒቨርሲቲ ሲገባ ግን እናቱ እንደገና ችግር ውስጥ ገቡ። ለሁለት አመት ያህል የዩንቭውርሲቲ ትምህርቱን ከተማረ በኋላ፤የገባው ነገር ቢኖር ከእናቱ ጋር አብረው ሲታገሉት የነበረው የዕለት የምግብና የኑሮ ፍጆታቸውን የሚያሟላ ገንዘብ ማግኘት ጉዳይ ከ3 ዓመት በኋላ እስከመጨረሻው መልስ እንደሚያገኝ ነበር።


ሁልተኛ ዓመት ሲደርስ ከዶርም ጓደኞቹ ጋር በመሆን አዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሰጠውን የግቢ ጉባኤ ትምህርት መከታተል በመጀመሩ ለዘመናት እንዲሁ ለመሳለም ብቻ ይሄድባት የነበረችው ቤተክርስቲያን ብዙ የማያውቃቸውን የሕይወት ምስጢሮች መያዟንና እግዚአብሔርም ለሰው ልጅ ያለውን የጸና ፍቅር እንዲረዳ ስላደረገው፤በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ተሰምቶት የማያውቅ ትልቅ ሐሴት ማግኘት ጀምሯል።አሁን ሰላምይሁን የሕይወትን ጣዕም መረዳት እንደጀመረ በልቡ ይሰማዋል፤ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ ማንበብ በመጀመሩና ከደርም ጓደኞቹ ጋር ስለትምህርት እና ስለመንፈሳዊ ህይወታቸው በየቀኑ መነጋገር በመጀመራቸው ጥዋት ጥዋት ለብሰውት ከሚሄዱት ነጠላ በላይ ልቡ በብርሃን እየትሞላ መሆኑን እየተረዳ ነው፤እግዚአብሔርም ሁሌ አጠገቡ ሆኖ እንድሚያናግረው ይሰማዋል። ይሁን እንጅ ደስታው የሁለተኛ ዓመት ትምህርቱን ሊያስጨርሰው አልቻለም። ሁለት ገምቷቸው የማያውቃቸው ከባድ ፈተናወች ሳይራሩለት አንድ ላይ ከፊቱ ተሰልፈዋል። በመጀመሪያ እናቱ ከዕለት ወደ ዕለት ሕመማቸው እየጠና መምጣቱን ሲነግሩት ልቡ አብዝቶ መጨነቅ ጀምሯል። ሁለተኛ የተፈጠርበት ችግር ከእነርሱ "department" ተማሪ ከሆነች ልጅ  ጋር እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሆነ ሊገልፀው በማይችል መልኩ ፍቅር ይዞት መሰቃየት ጀምሯል።


ወቅቱ የሁለተኛ ዓመት የመጨረሻ ፈተና የጀመረበት ከመሆኑ ጋር ተደምሮ በእናቱ የጤና ማጣትና ባፈቀራት ሰናይት ጉዳይ የሚያደርገው ሁሉ ተደበላለቀበት። ቢያንስ የሰናይትን ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት የፍቅር ጥያቄ አቅርቦላት ምላሹን ለማወቅ ብዙ ጊዜ ፈነልጎ ነበር፤ግን ሃሳቡን በደንብ መግለፅ የማይችልለት አንደበቱ እንኳን ለእርሷ ይቅርና ለመንፈሳዊ ወንድሞቹ ሊናገር ፈራበት። ስለፍቅር ከባድነት ሲሰማው የነበረው ነገር ሁሉ በእርሱም ላይ ደርሶ ሁለመናውን እንዲርድ ማድረጉ፣ለትምህርት ወደ ክፍል በገቡ ቁጥር እርሷን እያየ ትምህርቱን መከታተል አለመቻሉና ለንባብ ቤተ መጽሐፍት ሲገባ በሚያነበው መጽሐፍ ሳይቀር የእርሷ ምስል እየመጣ ማጥናት ስላቃተው ሕይወቱ አደጋ ውስጥ እንደሆነ እየተሰማው ነው። የሁለት መኪናወች መጋጨት ድንገት ከገባበት የሃሳብ ጉዞ የመለሰው ሰላምይሁን ትኩረቱ በሰወቹ ግርግር ላይ ከቆየ በኋላ ተመልሶ በራሱ መበሳጨት ጀመረ። "ለምን? ይሄ ሁሉ በእኔ ላይ!" አለ፤ግን ማንም የሰማው አልነበረም።"እሺ ቢያንስ ምናለ እናቴን ትምህርቴን እስከምጨርስ ድረስ ባታሳምምብኝ" አለ። ሰላም ይሁን በየቀኑ ከራሱ ጋር እያጣልው ያለው ነገር ሕክምናው ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ዐቅም በላይ በመሆኑ ወደ ውጭ ሄደው መታከም እንዳለባቸው መስማቱ ነው።


ፈጣሪን ለሁሉም ነገር መውቀስ ያምረውና መልሶ ደግሞ በዚህች የአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የተማረው ቃለ እግዚአብሔር ይሞግተዋል።"እንዴ እስከዛሬ ወደ ቤትህ ሳልጠጋ ምንም ያልሆንሁትን፤አሁን ስቀርብ ነው እንዴ! በፈተና  ብዛት ልታሳብደኝ የምትፈልገው?" ብሎ ብዙ ጊዜ እንደሰው ቤተክርስቲያን ፊት ቆሞ እግዚአብሐርን ሞግቶታል። ዛሬም ጭምር የሚወደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን መጥቶ፤ይህንኑ ለፈጣሪ ልንገር ብሎ አጠገቡ እንደሰው ቆሞ ነግሮታል። እናቱ የሚያማቸውን የኩላሊት በሽታ ወደ ውጭ ሃገር ሂደው ለመታከም ዶክተሮቹ የነገሩት ቀሪ ጊዜ አንድ ወር ከግማሽ ብቻ መሆኑን ነው። አስራ አምስት ቀኑ ደግሞ ተገባዷል። ሌላው አስቸጋሪ የሆነበት ነገር ጓደኖቹን እንዳያማክራቸው የፈተና ሰዓት በማጠናቀቃቸውና ትምህርት ቤቱ በመዘጋቱ ሁሉም ወደየመጡበት ሃገር ተመልሰዋል። መንፈሳዊ ወንድሞቹ "እርሷን ከመጠይቅህ በፊት እግዚአብሔርን ደጅ ጥና ፣የእርሱ ፈቃድ መሆኑ አረጋግጥ፣በዛ ላይ ተማሪ መሆንህን አትዘንጋ"።ስላሉት ጭንቀቱን ሁሉ እንደያዘ ነበር የሁለተኛ ዓመት የማጠቃለያ ፈተናቸውን ወስደው ከግቢ የወጡት። በምድር ላይ በማንም የማይተካውን ፍቅር የሰጡት እናቱ ታመው ባሉበት ሁኔታ እንኳን ሰናይትን ማሰብ ሊያቆም አለመቻሉ አንዳንዴ ሲገርመው አንዳንዴ ደግሞ ያናድደዋል።


ለእናቱ ህክምና የሚያስፈልገው "280,000 {ሁለት መቶ ሰማኒያ }ሺሕ ብር ከየት ይመጣል?" ብሎ ሲያስብ ሕሊናው ለፈነዳ ይደርሳል። ደግሞ ድንገት ኢዮብን ያስብና ይጽናናል። በቆመበት ራቡ ሲሰማው እናቱን ለማየት ለጊዜው ጨርቆስ ሰፈር ወደተከራዩኣት ትንሽ ቤት በፍጥነት ተመልሶ መሄድ ፈለገ፤ግን ደግሞ ምንም ተስፋ ያለው ነገር ሳይዝ የእናቱን ፊት መመልከት ሰቀቀን ይሆንበታል። ደቂቃወች በገፉ ቁጥር እናቱ ወደ ሞት አፋፍ እየተቃረቡ መሆኑን ያስብና የእርሱ ነፍስ ቀድማ ብትወጣ ይመኛል። ዘመዶቹ በሙሉ ከሃገር ቤት ከጥሪታቸው የቻሉትን ያህል ረድተዋቸዋል፤ሌላ ምንም ሊያደርጉለት ባለመቻላቸው ነገሮች ሁሉ ተመሰቃቅለውበታል። "ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ከሰማይ ተዓምራትህን አውርደህ፤አንተ ራስህ  የእናቴን ጤና ካልመለስክ መስተቀር እኔ ምንም ላደርግ አልችልም።"ብሎ ጮሆ ተናገረ። ድምፁ ከፍ ብሎ በመውጣቱ አጠገቡ ያሉት ሰወች በሃዘኔታ መልክ እየተመለከቱት ሲያልፉ ደንግጦ አይኑን የሚያሳርፍበት አጥቶ ሲንከራተት ድንገት ያየው ነገር ልቡን ቀስፎ ያዘው።የት እንደምትኖር እንኳን የማያውቃት ሰናይት መንገድ ተሻግራ ወደ እርሱ አቅጥጫ እየመጣች ነው።


ትምህርት ከተዘጋ በኋላ አይቷት ባለማወቁና በየቀኑ ሃሳቡ ከእርሷ አልለይ ብሎት ሲሰቃይ መክረሙ አንድ ላይ ተደማምረውበት ሲያያት እናቱ ወ/ሮ ብርሃንን ያገኘ እስኪመስለው ድረስ ልቡ ማልቀስ አማረው። አጠገቡ ደርሳ ሰላም ስትለው የተመለከትችበት ግራ የተጋባ ስሜት እርሷንም ስለረበሻት፤በማያቋርጡ ጥያቄወች አጣደፈችው፤ያለበት ሁኔታ ጥሩ አለመሆኑን ግን በድን በሆነ አካሉና ለምትጠይቀው ጥያቄ ሁሉ ደህና! ደህና! የሚል መልስ ሲሰጣት በመረዳቷ፤አጠገባቸው ወዳለው ካፌ ይዛው ገባች። ከክፍላቸው ውስጥ ጎበዝ ተማሪ እና ጨዋ ወንድ በመሆኑ በጥሩ አይን የምትመለከተው ሰናይት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራት ጠየቀችው። አጠገቡ የተቀመጠችው በእውነት ሰናይት ትሁን ወይ ራቡ አስክሮት እየቃዠ መሆኑን ተጠራጠረ። ሰላምይሁን ግራ ገብቶታል። "እናቴ በጠና ታማለች ሰናይት ልትሞትብኝ ነው.... እኔ እናቴን አጥቼ መኖር አልችልም።" ብሎ የቀረውን ኬክ ሳይጨርሰው እንደ ህጻን ልጅ ተንሰቅስቆ አለቀሰ። በእርግጥ እንደዚህ ያደረገው የእርሷ ሳያስበው አጠገቡ መገኘቷ ነበር።


ሰናይት ቤተሰቦቿ ስለክርስትና ሕይወት ጠንቅቅቀው ያስተማሯት በመሆኑ የሰው ሃዘን ቶሎ ይገባታል።"በቃ በእናትህ አታልቅስ ሁሉም ነገር መፍትሄ አለው፤አንተ ተረጋጋ" ብላ ልታጽናናው ሞከረች። ሁሉንም ነገር ጠየቀችው። ሰላም ይሁን ለራሱ እስኪገርመው ድረስ ስለራሱና ስለቤተሰቡ ሁኔታ፣ስላሳለፈው ታሪክ አንድም ሳይደብቅ ነገራት። ወዲያው ግን የገረመው ነገር ለዶርም ጓደኖቹና ለመንፈሳዊ ወንድሞቹ ሳይቀር ነግሯቸው የማያውቀውን ታሪኩን ለእርሷ ነግሯት ከጨረሰ በኋላ በሕይወቱ ውስጥ ተሰምቶት የማያውቅ የሸክም መቅለል ስሜት የተሰማው መሆኑ ነው። ታሪኩን ነግሯት ከጨረሰ በኋላ ሳያስበው ፈገግ አለ፤እግዚአብሔር ለእርሱ የሆነ ነገር ሊያደርግ እንደፈለገ በልቡ ውስጥ እየተሰማው ነበር። ሰናይት ሰምታ እንደጨረሰች ምንም ሳትለው ጸጥ ብላ ለርዥም ሰዓት በፈገግታ እየተመለከተችው ስለቆየች ግራ ገባው።በመጨረሻ ከአፏ የወጣው ቃል "እግዚአብሔር በስራው ሁሉ ድንቅ ነው" የሚል ነበር። ግራ ተጋብቶ አያት። "የሚገርምህ በልቤ ምን እያሰብሁ እንደነብር ታውቃለህ?" አለችው። ራሱን በመወዝወዝ የምትለው እንዳልገባው ሊያሳያት ሞከረ።


 "የሚገርምህ ዛሬ ጥዋት ከቤተክርስቲያን ተመልሼ ቤት እንደደረስኩ ከዚህ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቅ አይነት ጭንቀት በልቤ ውስጥ ተሰማኝ፤በቃ ከቤት ውጭ ሂጅ ሂጅ የሚል ከባድ ስሜት ነበር። የት እንደምሄድ ግን አላውቅም ነበር፤ ከዚያ ታክሲ ይዤ ያለ ምንም ምክንያት ከአስኮ ወደ ፒያሳ መጣሁ" አለችው። ሰላምይሁን ሰናይት በምታወራው ነገር ልቡ ስለቆመ ይበልጥ በጉጉት ያዳምጣት ጀመር። እግዚአብሔር በእናቱ ጉዳይ አንዳች ነገር ሊያደርግ መፈለጉን አሁን ይበልጥ እርግጠኛ እየሆነ ነበር። ምክንያቱም ሰናይት ድንገት እንዳልተከሰተች ገብቶታል። በቃ እግዚአብሔር እርሷን ልኳታል። በልቡ "ጌታ ሆይ እባክህ የነገርሁህን ሁሉ አንተ ታውቃለህና ይህን ሁሉ ታሪክ የሚቀይር ነገር ስራ" አለ። ፈገግታ በተሞላበት ፊት አሁንም "የእግዚአብሔር ስራ የሚደንቅ ነው" አለችው፤"ደግሞ እንዴት?" አላት። "የሚገርምህ ሰሞኑን በተደጋጋሚ አንድ አይነት ህልም እያየሁ ነበር። እና ሄጀ ለንስሐ አባቴ ስነግራቸው ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ?" በጭንቀት መንፈስ ጠጋ ብሎ አያት። "ሰሞኑን የሚጠብቅሽ ልዩ እንግዳ አለ፤ስለዚህ ምንም ሳታመንቺ በደንብ አስተናግጂ" ብለውኝ ነበር። "የሚገርምህ የዚህን ሕልሜን ምንነት አሁን አንተን ሳገኝ ነው የተረዳሁት፤ለዚህ ነው የገረመኝ" አለችው።"እንዴት ማለት?" ይበልጥ ግራ ገባው ሰላምይሁን።


"ቤተሰቦቼ በሙሉ ሚኖሩት አሜሪካን ሃገር ነው፤ረዥም ጊዜ እዚያው በመቆየታቸው ሁሉም ዜግነት አላቸው። "እና ምን ይሁን  በሚል አይነት ሁኔታ ተመለከታት።"እና ሰሞኑን ክረምቱን እነርሱ ጋር እንዳሳልፍ ለእኔ የግብዣ ወረቀት ከአንድ ሰው ጋር ነይ ብለው ልከውልኛል፤አብሮኝ የሚሄድ ማን ነው? ብየ ስጨነቅ ነው፤ይህን ህልም በተደጋጋሚ ያየሁት። ዛሬ ጥዋት ደግሞ በጣም ጨንቆኝ ከቤት ወጥቸ ስመጣ ካንተ ጋር ተገናኘሁ፤ ይህ አይገርምም?" ሰላምይሁን የሚለው ጠፍቶት እንባ ባቀረሩ አይኖቹ ሰናይትን ከማየት ውጭ የሚለው ነገር አልነበረውም "የሚገርምህ እኮ ደግሞ ቤተሰቦቸ ሁሉ በህክምና ሙያ ላይ ያሉ መሆናቸው ነው፤በተለይ ትልቋ እህቴ ሰውን እንደመርዳት የሚያስደስታት ነገር የለም" አለችው። ሰላምይሁን ከብዙ ምጥ በኋላ "አሁን የምትነግሪኝ ነገር የምርሽን ነው? ወይስ እየቀለድሽ ነው?" አላት። "ማለት?"አልችው ትንሽ ቆጣ ብላ።"አይ ማመን ተስኖኝ ነው፤ይህን ያህል ገንዘብ የሚጥይቅ ነገር እንደ ቀላል የሚሳካበትን ነገር ስትነግሪኝ ምን ልበል አላት"። "አትሳሳት ይህን ሁሉ ያዘጋጀው ራሱ እግዚአብሔር ነው። ምክንያቱም የአሜሪካ ኢምባሲ የግብዣ ወረቀት ከሌላ አንድ ሰው ጋር እንድትጓዝ እድል የሚስጥህ ከስንት አንድ ጊዜ ነው" አለችው።


"ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም....ብቻ ሰናይት እግዚአብሔር ድንቅ ነው ለካ እንደ ኢዮብ በፈተና የሚጸና ሰው ከእዚአብሐር መልስ ያገኛል" አላት። ከተቀመጡበት ካፌ እንደወጡ በቀጥታ እናቱ ወዳረፉበት ቤት ነበር አብረው የተጓዙት፤ በእያንዳንዱ የእግሩ እርምጃ ልክ እግዚአብሔር በስራው ሁሉ ምን ያህል ድንቅ አምላክ መሆኑ እያሰበ ነበር፤በጥንት ዘመን ለእስራኤላውያን በምድረበዳ መናን ከሰማይ ያወረደ አሁን ደግሞ በእርሱ የኑሮ ደረጃ ሊፈታ የማይችለውን የእናቱን ከባድ ችግር ሊፈታ ተዓምራቱን እየገለጠ መሆኑ ተረዳ። አሁን ሁሉም ነገር እንደሚቻል ስለገባው "ለምን? ይህን ሁሉ መከራ በእኔ ላይ!" ብሎ ያማረረበት አንደበቱ እያሳፈረው ቀንና ሌሊት በፍቅሯ ወጥመድ ውስጥ ካስገባችውና የዛሬዋ ደግሞ የእናቱ ሕይወት ታዳጊ ከሆነችው ሰናይት ጎን ሆኖ የቸርችርን አደባባይ ቁልቁለት ተያያዙት፤ በልቡ መንገዱ የእርሱ ሕይወት እየመሰለው።
               

                                                                         ምንጭ፦ጉባኤ ቃና ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
                                                                                    የካቲት 2005 ዓ.ም

2 comments:

  1. በጣም ይገርማል! እግዚአብሔር ሆይ ስራህ እጅግ ድንቅ ነው፡፡ የታየሪኩን መጨረሻ እስካውቅ ድረስ የእናቱ ህመም የልጅቱ ፍቅር የልጁ ጭንቀት እኔንም በጣም አስጨንቆኝ ነበር፡፡ ለካስ እግዚአብሔር እኛ በማናውቀው መንገድ ሁሉ ድንቅ ስራውን ይሰራል፡፡

    ReplyDelete
  2. በጣም ይገርማል! እግዚአብሔር ሆይ ስራህ እጅግ ድንቅ ነው፡፡ የታየሪኩን መጨረሻ እስካውቅ ድረስ የእናቱ ህመም የልጅቱ ፍቅር የልጁ ጭንቀት እኔንም በጣም አስጨንቆኝ ነበር፡፡ ለካስ እግዚአብሔር እኛ በማናውቀው መንገድ ሁሉ ድንቅ ስራውን ይሰራል፡፡

    ReplyDelete