Friday, November 27, 2015

ጥጡና ፈታይዋ

ባበባነት ወቅቱ
ጥጥ ነኝ ብሎ ቀርቧት
ፈታይ ሆና ቀርባው
ከስሩ ፈንቅላው
ከንቡጡ ፈልፍላው
ከ'ማረጉ አውርዳ
መሬት አስተኝታው
በፈገግታ በትር በሳቅ ማዳወሪያ
ቀኑን ሙሉ ወቅታው
በድምጧ መንደፊያ
ባ'ይኗ መዳመጫ
ከፍሬው ለይታው
ለካ እሱም ተረቶ
ሰውነቱን ትቶ
{አምኖ ጥጥነቱን}
መዳፏ ስር ገብቶ
ድድር ገላው ላልቶ
ኾኖላት ባዘቶ
በስሜት እንዝርቷ
ታብቶላት አስራው
በራቁት ጭኗ ላይ
አሽከርክራ አሹራው
ሲወፍር አቅጥናው
ሲረግብ አክርራው
ሲያሰኛት ልቃቂ
ሲያሻት ቀለም አርጋው
ለካ እሱም ተረቶ
ሰውነቱ ትቶ
ጥጥነቱን አምኖ
እንዳደረገችው እንዳሰኛት ሆኖ
መለወጡን እንኳ ሳያስብ ላንድ አፍታ
ከጥጥነት ልቆ ሆኗት ቀጭን ኩታ
ቀነቀን ለውበቷ
ማታ ለሙቀቷ
ሲሆን ሰነባብቶ
ዕድፍ እና ትቢያ ከገላዋ አንስቶ
ጸዐዳው አከሉ እያደር ጨቅይቶ
እሷ ሳትለውጥ
እሱ ነትቦ አርጅቶ
ተሽቀንጥሮ ቀረ ሆነና ቡትቶ
በሌላ ጸዐዳ ኩታ ተተክቶ
                   ስብስብ ግጥሞች
                            በውቀቱ ስዩም

No comments:

Post a Comment