Thursday, April 23, 2020

...ፍረደን...

ስማኝማ አንድዬ
ስድስት ሺህ ጅራፍ ተቆጥሮ የማያልቅ ስፍር የለሽ በደል
ለከፈልክባት ቀን እንኳን አደረሰህ አይባልም አይደል
.
የሰማዕታት ሀገር የፃድቃን ከተማ
ፅርሐዓርያም እንዴት ነው በበዓል ዋዜማ
ከዙፋንህ ግርጌ ቄጤማ ጎዝጉዘው እያሸበሸቡ
ሰውና መላእክት በአንድ ሲሰባሰቡ
ከመላእክት ምግብ ፃድቃን ሲመገቡ
ሰማይ ቤት እንዴት ነው የበዓል ድባቡ
.
ትዝ ይልሀል አይደል ?
አልጋውን አስይዘህ ያ'ዘለልከው ድኩም
አላውቀውም ብሎ የመታህ በኩርኩም
እንዴት ነው መፃጉ ኑሮ እንዴት ይዞታል
ቸርነትህ ደርሶት እርሱም ገነት ገብቷል
ወይስ የሲዖል ፍም እሣት ተስማምቶታል
.
ኑሮ ከተባለ እኛ አለን እንዳለን
አንተን መስለንና ያንተን አስመስለን
እንደ ኮሶ እንደ ሬት ኑሮ እየመረረን
እኔን ምሰሉ ሚል ቃልህን አክብረን
ሰውን ያክል ክቡር ነፍስ ተሸክመን
ፈውስ ያልተገኘለት new virus አክመን
አድናለሁ ስንል እራሳችን ታመን
.
ሰርዷችንን ግጦ የጠገበ ኮርማ ዞሮ እየረገጠን
ወርቅ የሰፈርንለት አመድና ትቢያ አፈር እየሰጠን
ኑሮ ከተባለ እኛ አለን እንዳለን
አንተን መሆን ባንችል ያንተን አስመስለን
.
እናልህ አንድዬ
እንዳይጎርስ ለጉመው እንዳይሄድ ቀይደው
ቤቱ  እንዳይቀመጥ በሥራ ጥመደው
የሚል ህግና ደንብ ከልካይ አዋጅ ወጥቶ
ተመጥምጦ አለቀ ጉልበታችን ሟሙቶ
.
በራሳቸው ችሎት
ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ዳኛ ሆነው እየቀጡን
ውኃ ጠማን ስንል ሆምጣጤ እያጠጡን
ከኩንታል ሙሉ ማር ሸክማችን ከበደ
ወዳንተ እንዳንመጣ ጉልበታችን ራደ
እንደ ልባሽ ጋቢ ዋጋችን ቀለለ
እባክህ ቶሎ ና ትክሻችን ዛለ
.
ልብሳችንን ነክተው ደማቸው ቀጥ ያለ ከሞት የተረፉ
ሀኪም ድሮ ቀረ እያሉ ለፈፉ
በእኛ መስዋዕትነት ከመቅሰፍት የዳኑ
በፈውሳቸው ማግስት እኛ ላይ ጀገኑ
 .
መንግሥት!?
መንግሥትማ አለ እንጅ ስራውን ይሰራል
ዘላለም የመንገሥ መብቱን ያስከብራል
የተቃዋሚውን ጀርባ አጥንት ይሰብራል
በጠብመንጃው አረር የደቀቁ እግሮችን ሆስፒታል
ይልካል
እንቶኔና እንትና በፈጠሩት ግጭት እያለ ይሰብካል
.
ተሰባሪው ታዲያ ሰባሪውን ፈርቶ አዳኙን ይከ'ሳል
የሀኪሞች ስህተት ውጤት ነው እያል አቧራ ያስነሳል
በርግጥ ሰው ይስታል እውነቱ አይካድም
በማካሮ ሽጉጥ መስበሩ ባይከብድም
ለዜና ካልሆነ
የተሰበረ እግር በጥገናው ማግሥት ቆሞ አይራመድም
.
እናልህ አንድዬ
በዚች የጉድ ሀገር ባልታደለ ዘመን በጉድ ወቅት ተፈጥረን
አንድ ቀን ከግማሽ ያለምንም ዋጋ ዱቲ ተወጥረን
ሥራ አጥ በሚል ማዕረግ ኩንትራት ተቀጥረን
በእለተ ትንሳኤ ላባችን ገብረን በደማችን ሰክረን
ካሣ' ሙሉ ፈጅቶ የመጣ ሰካራም እያደነቆረን
ልዝብ ያልከው ቀንበር ሸክሙ ከበደን
ነፃ አውጭ ላክልን ወይ መጥተህ ፍረደን
.
 (መታሰቢያነቱ፦ የትንሳኤ በዓልን ከቤተሰብ ተለይታችሁ ሆስፒታል ውስጥ ለምታሳልፉ የጤና ባለሙያዎች በተለይ በአውደ ዓመት ምድር ያለምንም ክፍያ ላብና ደማችሁን ለምትገብሩ ኢንተርን ሀኪሞች እንዲሁም ምንም ነገር ባልተሟላበት ሁኔታ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ለምትዋጉ የጤና አርበኞች ይሁንልኝ ።)

Tuesday, March 17, 2020

ፀባይ

“ቢያንስ በፀባይ ማስተናግድ ትችል ነበር” ይለኛል የማንም ወመኔ የቤቱን ጉድ ሁሉ አግተልትሎ እየመጣ
.
ለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ያለን ኢትዮጵያዊ  ሀኪሞች ከሌላው ሰው የተለየ ትዕግስትና ትህትና እንዲኖረን የሚጠበቀው ለምንድን ነው? አስራ ስምንት ዓመት ሙሉ ተምረን ስለምትከፈለን ለቤት ኪራይ የማትበቃ ደመወዝ (6179) ነው ? እንደ ጅብ ሌሊቱን ሙሉ ስንጓዝ አድረን ስለምናገኛት ለዚያውም በስንት ልመና ስለምትመጣው የተረኝነት አበል ነው? የላቦራቶሪ ግባቶችና የህክምና መሳሪያዎች በሌሉበት አስታማሚዎቹ ሲያለቅሱ አብረን ከማልቀስ ውጪ ምንም ማድረግ በማንችልበት ባዶ ህንፃ ውስጥ ተቀምጠን የጤና መድህኑን ብቻ አንጠልጥሎ የመጣን ከሞት አፋፍ ላይ ያለ ታካሚ እያየን  ስንጨነቅ ስለምንውል ነው? ቆይ ምን አድርጉ ትሉናላችሁ ?
.
ሁሉም በየቤቱና በየመሥሪያቤቱ ጉዱን አስቀምጦ “ሆስፒታል” ሲመጣ እራሱ ላይ ፈልጎ ያጣውን ጨዋነት ሀኪሙ ላይ ካላገኘሁ ሞቼ እገኛለሁ ይላል። ስታሳድገኝ ያላስተማርከኝን ጨዋነት ከየት እንዳመጣው ትፈልጋለህ? ያኔ አስፓልት ላይ አንበርክከህ እንደ ሌባ አርባ ጊዜ አስገርፈኸኝ ዛሬ ለምን ፊትህን አጠቆርክብኝ ብለህ ያዙኝ ልቀቁኝ ስትል ትንሽ አይሸምምህም? ሂድና ይችን ምርመራ አስረትህ ና እምቢ ነው! ይችን መድሃኒት ከውጭ ግዛና ውሰድ “ያንተ መነገጃ አድርገኸኝ” ነው! የላቦራቶሪና የህክምና መሳሪያዎች ይሟሉልን ብለን ጥያቄ ስናነሳና ድምፃችንን ስናሰማ ህዝብና መንግሥት እየተቀባበሉ “ሀኪሞች ጠግበው ሥራ አቆሙ” ነው ። “ልትወልድ የመጣች እናት ትተው ሰልፍ ወጡ” ነው። ባልታደለ ዘመን በግም ወቅት ተፈጥረን በሁለት ወጥመድ የተያዘች ቆቅ ሆነን አርፍናትኮ ጎበዝ !!!
.
©ዶ/ር ጌታነህ ካሴ
ፍ/ሠላም ሆስፒታል

ዘመቻ

አንት የኮስትር አሽከር የቴዲ አልጋ ወራሽ ስማኝ ወንድም ጋሸ
በለስላሳ አንደበት በቅቤ አንጓች ምላስ ቀርቦ እያሞካሸ
ሊያጀልህ ቢሞክር የማንም ወስላታ
አቤት ወዴት ብለህ ትጥቅህን አትፍታ
ሚስትህን ከሽፍታ ታግለህ እንድታስጥል
ሽመል ከዘራህን ከክንድህ አትነጥል
እምቢ በል ጀግናዬ ፎክር እንደ አባትህ
በባንዳ ከሃዲው በሰላቶው ሁሉ አይደፈር ቤትህ
አስከትለኝና ዝመት ወደ ጫካው እንሂድ ወደ ጋራው
በክንድህ ብርታት ነው የነፃነት ጮራ ፀሐይህ ሚያበራው
ልጅህን ተዘርፈህ ምንድን ነው ዝምታ
ክንዳለሜ እያለች እህትህ ታግታ
ውርደትን ታቅፎ ምንድን ነው ምኝታ
እስከ መቼ ትዕግስት እስከ መቼ ዛቻ
እስከ መቼ ድረስ የቃላት ጦርነት የስድብ ዘመቻ
እንዲህ የጭንቁ ዕለት
እንዲህ በክፉው ቀን ልብህ ካልጨከነ
ሦስት ዙር ዝናርህ ምኑን ዝናር ሆነ
ምኑን ነፍጠኛ ሆንክ ምኑን ትምክህተኛ
በርህን ሲቆረቆር አጥርህ ሲነቀነቅ ልብህ እየተኛ
.
.
.
ወይ ነዶ

Tuesday, December 31, 2019

???


ግዳይ አስቀምጦ ለሕይወት መታጨት
ዘር ቀለም ሳይመርጡ ሰው ከእንስሳ መቅጨት
ፀሐይ ቁር ሳይፈሩ ግዑዝ ሆኖ ማርጀት
ጠፋች ሞተች ሲባል
ሰላም ለከ ብሎ ዳግመኛ መደርጀት
አጥፍቶ አለመጥፋት ልምድሽ ሆኖ ኑሮ
ኑሮ ኑሮ ኑሮ
ካንቺም በላይ ጀግና ሲመጣ ሲፕሮ
ቁርባ ቁርቢት ቁርጥሽ ነው ዘንድሮ

ቱ!

ያልታደለች ጉብል እድል የጠመማት
በአመንዝራ ዲያቆን
ተደፈርኩኝ ብላ ነገሩ ሲገርማት
የነፍሷ ጠባቂ ካህኑም ደገማት
በየት በኩል አልፎ ፈጣሪዋስ ይስማት?
ቱ!

Sunday, December 15, 2019

ጭንቃጭንቅ ዜና


በማድጋ ዞን ሽንክላ ወረዳ ጭንቁላ ቀበሌ የሽንትቤት ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ዋለ።

አ.ዲ.መ.መ ዘለፋ 8/900010 ዝንጠላ፡ ዲስኩር። በማድጋ ዞን ሽንክላ ወረዳ ጭንቁላ ቀበሌ የሽንትቤት ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ መዋሉ ተገለጸ። የቀብሌው ሊቀመንበር አቶ እንዳመጣው ደባልቄ በበዓሉ ላይ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደተናገሩት የዘንድሮውን በዓል ከባለፉት ለየት የሚያደርገው ከምንትስ ሚሊዬን በላይ ሶፍትና ወደ ብጥስጥስ የሚጠጉ የሽንት ቤት ወረቀቶችን ለማከፋፈል የቻልንበት መሆኑ ነው ብለዋል ። በበዓሉ ለረዥም ስዓት ሽንት ቤት ውስጥ በመቀመጥ የተሻለ ልምድ ላካበቱ ሞዴል ሽንታምና ተቅማጣም ወጣቶች የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ሌሎቻችንም የእነዚህን ግንባር ቀደም ወጣቶች አርዓያ ልንከተል እንደሚገባ ተጠቁሟል። ከተሸላሚ ቤተሰቦች አንዷ የሆኑት ወይዘሮ ትንጓለል አዝብጤ በበዓሉ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በቅርቡ የሚከበረውን የወስፋትና ወስፋታሞች ቀን ለማክበር ዝግጅት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ከዜናዎቹ ጋር እሣቱ ለብልቤ ነበርሁ ሰላም

ኑሮ ተወደደች ደስታ ተሰደደች
እኔ እበላው ሳጣ ሚስቴ ልጅ ወለደች
ስኳር ጣሪያ ነካ
ግፊቴም ከፍ አለ ብላችሁ ምትፈሩ
ተካፍሎ ማደር ነው የጤና ምስጢሩ
መልካም ዕለተ ሰንበት