Sunday, May 15, 2016

ለአንቺ


ባህር ወደታች ምን ያህል ጥልቅ ነው? ዓለምስ ወደጎን ምን ያህል ይሰፋል? ፀሐይ ምን ያህል ትርቃለች? ከዋክብት ምንኛ ይበዛሉ? የሰው ልጅ ልቦና ምን ያህል ርቀት ይመሰጣል? አእምሮው እስከየቱ ጥግ እስከምን አጥናፍ ድረስ ያስባል? ሁሉም ወሰን አለው። ሁሉም ዳር ድንበር ጥግ አለው።ምድር ምንም ፍጹም ነገርን እንደማታስተናግድ ትባላለች። ፍጽምና የለባትም ይባላል። ሁሉም ጎዶሎ እንደሆነ ይነገራል። ሁሉም ሙሉ ለመሆን አንዳች ሌላ ግብዓት ይሻል። ቀን ያለፀሐይ፤ ምሽት ያለ ጨረቃና ከዋክብት፤ ዝናብ ያለደመና፤ ደስታ ያለመከራ፤ ድል ያለውጊያ አይገኙም። ዓለም ራሷ ምኗም ሙሉ አይደለም። አንዱ ከአንዱ ጋር ይደጋገፋል።ትዕግስት ጠረፍ አለው፤ ጽናት ገደብ አለው፤ ሸክም ልክ አለው። የሰው ልጅ «ከዚህ በላይ አልችልም፤ ከዚህ በላይ አልታገስም፤ ከዚህ በላይ ይከብደኛል» የሚለው ጠርዝ አለው። ይደክማል። ይሰለቻል። ቢታገስ እንኳን ያማርራል፤ ቢጸናም ተስፋው ይዝላል፤ ቢሸከምም ደርሶ አውርዶ ሊጥል ይናፍቃል።ሰው ስልቹ ነው። ሰው ወረተኛ ነው። ዛሬ የያዘው ወርቅ ነገ መዳብ ይመስለዋል። ዛሬ ያመሰገነውን ነገ ሊኮንነው ይችላል፤ አሁን ለሳቀለት አፍታም ሳይቆይ ይነክሰዋል። ሰው ወረተኛ ብቻ አይደለም። ደግሞም ራሱን ወዳድ ነው። ለእርሱ እንደተመቸው ብቻ፤ ለእርሱ እስከሆነለት ብቻ ነው ምንም ነገር ቢሆን የሚፈልገው።

Saturday, April 30, 2016

አደናጋሪው ጩኸት !

መላዋ እየሩሳሌም የጩኸት ድምጽ ይሰማባታል፤ከወትሮዋ በተለየ ሁኔታ ጩኸት በዝቶባታል። ከወዲያ ወዲህ እየተመላለሱ ህዝቡን የሚያሳምፁ ካህናቱና ሊቃነ ካህናቱም ወገባቸውን ታጥቀው ይመላለሱባታል። የከተማዋን ሽብር የተመለከቱ ሁሉ  የገበያ ቀን ነበርና ግራ ተጋቡ በሚሰሙት ጩኸት ተደናገሩ፣የጩኸቱን ምክንያት ተረድቶ ማስርዳት የሚችል ግን አንድም ሰው የለም ብቻ ሁሉም ይጮሃል። በመንገድ አልፈው የሚሄዱትም "ቤተመቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምተሰራው"  እያሉ ይጮሁ ነበር። ከቤተ መንግስትም ሆነ ከቤተ ክህነቱ ባለስጥናት  ጩኸቱን ለማስቆም  የደፈረ ማንም የለም። ሦስት ዓመት ከሦስት ወር በተደረገው ተዓምራት በሕሙማን አድረው ይጮሁ የነበሩ አጋንንት ዛሬ ደግሞ በአይሁድ ልቡና አድረው ይጮሃሉ። ጩኸቱ ግን ይለያያል። ያን ጊዜ" ልታሳድደን መጣህን? "የሚል ሲሆን ዛሬ ግን "ስቀለው! ስቀለው!" የሚል ሆኗል። ነገሩ እየጠነከረ መጥቶ የጩኸቱ ምክንያት የሆነው ንጉሠ አይሁድ ኢየሱስ ክርስቶስ ታስሮ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ደርሰ። 


ሊቀ ካህናቱ ሀና የሥልጣን ዘመኑን ጨርሶ ለቀያፋ ያረከበ ቢሆንም ስለሽምግልናው በጀመሪያ በተከሳሹ ላይ ፍርድ እንዲሰጥ የተጠየቀው እርሱ ነበር። ነገር ግን እርሱም ቢሆን ጩኸቱ ለማስቆም አቅም አልነበረውም። ሲጀመርም ጩኸቱን መርቆ የከፈተው ማን ሆነና? የእርሱ የልጅ ባል ቀያፋ አይደለምን? "ስለ ህዝቡ ሁሉ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል" ብሎ። በዚህ በሊቃነ ካህናቱ የተጀምረው ጩኸ ወደ ሕዝቡ ወረደ በሊቀ ካህናቱ ግቢ የፍርድ ሂደቱ እየተካሄደ ባለበት ወቅት  ሌላ አዲስ ጩኸት ተከሰተ ፤የሰባኪው ዶሮ ጩኸት ተከሶ የመጣው  የክርስቶስ ፍርድ ሳይጠናቀቅ ደቀመዝሙሩ ዼጥሮስም ተከሶ ቆመ። በሕሊና ዳኝነት ወንጀለኛ መሆኑ ስለተረጋገጠ ምስክር እንኳን ሳያስፈልገው እራሱ በሰጠው የእምነት ቃል ማስረጃነት ዳኛው አስቸኳይ ውሳኔ ስለሰጡ ዼጥሮስ ስለራሱ እያለቀሰ ወጣ። ምንላባትም የጩኸቱ ምስጢር ገብቶት ስለራሱ ይጮህ የነበረ ብቸኛ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ሌሊቱን በሙሉ አንድ ጊዜ እንኳን ሳይተኙ በጩኸት ከሐና ወደ ቀያፋ ከቀያፋም ወደ ሐና እያመላለሱት ሲጮሁ አደሩ። ሲነጋም የካህናት አለቆች ከህዝቡ ሁሉ አሉ የትባሉትን ሽማሌዎች ጠርተው የሞቱን ጦማር አጸደቁት ። ከሳሽ ሳይኖር በደሉ ሳይዘረዘር  እንዲሞት የተወሰነበት የመጀመሪያ ሰው።

Tuesday, April 26, 2016

ሀቁን ካንቺ ልስማ

ሰላም ላንቺ ይሁን ለንጽህት እናቴ
ሳዝን መጽናኛየ ስደክም ብርታቴ፣
የመኖሬ ምስጢር የህይወቴ አንድምታ፣
ከሰማይ የተላክሽ የንጉሥ ስጦታ ፣
አማናዊት መርከብ ምሥለ ጎልጎታ፣
የሸክሜ ማቅለያ የምስጢር ዋሻዬ፣
ከጭንቀት ማምለጫ ጥላ ከለላዬ፣
ሰላም ላንቺ ይሁን ሰላም ነሽ እማዬ?
የምነግርሽ አለኝ ጆሮ ስጭኝ እማ!
እኒያ ጡት ነካሾች ሲሰድቡሽ ብሰማ፣
ውስጤ ተቃጠለ ሕሊናዬ ደማ፣
እውነቱን ንገሪኝ ሀቁን ካንቺ ልስማ፤
እውነቱን ንገሪኝ ሀቁን ካንቺ ልስማ።
ምን ጥፋት ሰርተሽ ነው? ምን በድለሻቸው?
አሻግረው ስላዩሽ ሚያንገሸግሻቸው።
ቆይ ምን ብተሰሪ ነው?
እኮ ምን ሰርተሽ ነው? ምንድን ነው ነገሩ?
እናጠፋታለን ብለው ሚፎክሩ።
ለምስጢር ያልበቃሁ ብሆንም ጎስቋላ፣
ትዕዛዝሽን ያልጠበቅሁ አደራ ምበላ፣
አፈር ትቢያም ብሆን ቢበዛም ሀጢአቴ፣
ቃላት መገጣጠም ባይችል አንደበቴ፣
እውነቱን ልወቀው ንገሪኝ እናቴ፤
እውነቱን ልወቀው ንገሪኝ እናቴ።

Sunday, March 27, 2016

አንደበት እና ጾም !

የተከበርክ ምላሴ ሆይ፡አርምሞን ገንዘብ አድርግ።አንተም ብዕረ አርምሞ የሚል ቃልን ጽፈህ ልቦናየን ለሚያውከው  ለዓይኔ መልእክት እንዲደርሰው አድርግ።ሥጋየ ፈቃድ በተነሳበት ጊዜ የጌታየን፣የፈጣሪዬን መከራውንና ግርፋቱን አስብ ዘንድ  ልቦናየ ይህን እያሰበ  እንዲበረታ እንዲህ ከሆነ ለዓለማዊ ህይዎት ሙት እሆናለሁ።ሣጋዊ ምኞትና ፍላጎት በነገሰበት ሕይዎት ለ አርባ አቅናት እንደ ጌታ ት ዝዛና ሕግ ልቡናዬን በንጽህና ለመጠበቅ ይቅርታ ለሚያሰጠው ህይዎት የተገባሁ እንድሆን።የ አባቶችን ምክር እቀበላለሁ፣የቅዱሳንን ፍኖት እከተላለሁ በከንፈሮቼ ላይ መዝጊያን አኑር ምክን ያቱም ብዙ መማር ስለሚገባኝ ነው  የምናገራቸውን ቃላርት እመጥን፣ሰውነቴን ለመቆጣጠር እችል ዘንድ፤ አንደበት የነስን ሩጫ ያሳድፋልና ሞገደኛ በሆነ የጻለ ሾተል ሰዎችን የሚገድል ሰው በቀላሉ ትንሽ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ያንበረክካል።ክንፍ ያላትን ከወጋች የንማትነቀለውን የምላስ ጦር የወረወረ ሰው(በ አላማም ያለ አላማም)አላማውን አይስትም።የቀረቡትን ሁሉ ያቆስላል ፤የመረዘውን ሁሉ ይገድላል።በጾም ወራት ሕሌና ፍጹም መረጋጋት ያስፈልገዋል።ከምድራዊ ሃሳቦች ሁሉ የጸዳ ከሰዎች ተለይቶ ብቻውን ከ አምላኩ ጋር የሆነ ሊሆን ይገባል።ሕሊና የኃዘን ደመና ሊያንዣብብበት ይገበዋል። ውጤቱም እርጥበት እንባን የሚያስከትል መራር ኃዘን ነው።


 ታላላቅ ነገሮችን ለመቆጣጠር የሚፈልግ ሰው ትንንሽ ነገሮችን መቆጣጠር ይኖርበታል። የምላሴን ኃይል ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር  ያለብኝ ከንፈሮቸ ምንም አይነት ቃላት እንዳያፈሱ ተስፋ አድርጌ  ለሰው ልጆች መርዙ የማይነቀል ገደይ እንደ ምላስ ያለ የለምና ነው። ምላስ ዘወትር ግልቢያን እንደሚናፍቅ  ከፊት ለፊት ያለውን ሁሉ ቀድሞ ለማለፍ እንደ ሚጋልብ ፈረስ ነው። ምላስ የተዘጋጀ የተደገነ ቀስት ነው። ሁሉን ማየት የሚቻለው ማን ነው? እጅ በአቅራቢያ የሚገኘውን ትንሽ ነገር በቀላሉ ይጨብጣል ፤እግርም ሁሉንም የመሬት ክፍል አይረግጥም፤አይንም ሰሜንና ደቡብን አይመለከትም፤ምላስ ግን የማይደርስበት ቦታ የለም። ምድርን ሁሉ ያካልላል ለነፍሰ ገዳዮችና ጣኦትን ለሚያመልኩ፣ሐሰትን ለሚዎወዱ አድጋ ነው በእብደታቸው ላይ ሌላ እብደት ይጨምርላቸዋልና። የፈጠነን ምላስ ሊያስቆም የሚችል ምድራዊ ኃይል የለም። ለመናገር የቸኮለ ከንፈርንም እንዲሁ ሰውም ቢሆን ውሽንፍርም ቢሆን፣የበረዶ ግግርም ጎርፍም፣ተራራም ቢሆን ባለ ቀስቱ ቅርብ ነው። ቀስቱ የተደገነ ነው፤ቀስቱ በደጋን ላይ ነው። አንድ ጣቱን ደጋን ላይ አድርጎ  አክሮ ቀስቱን ይወረውራል፤በረው የታለመላቸውን አላማ ይመታሉ። ሰማያዊያን ምድራዊያንም ቢሆኑ አያመልጧቸውም። ሕያዋንንም ሙታንንም ያለፉትን የሚኖሩትንና የሚመጡትን ሁሉ ይገድላል። የምላስ ቀስት እንዳይወረወርባቸው የሚጥብቁትንም የማይጠብቁትንም የተጣላቸውንም ወዳጆቹንም አይምርም።

Wednesday, March 16, 2016

አቤት ቆሻሻ !

በሀገራችን የዘመን አቆጣጠር ከ1980ዎቹ አጋማሽ አስከ1990 ዎቹ አጋማሽ ድረስ አልፎ አልፎ አዲስ አበባ ስታዲየም መግባትን አዘወትር ነበር ። በተለይ ብሔራዊ ቡድናችን ጨዋታ ሲኖረውና ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ግጥምያ ሲኖራቸው አልቀርም ነበር ።ታዲያ በስቴድየሙ ቆይታዬ የሚያረካኝ ከጫወታው ይልቅ ከመስመር ያልወጡ የደጋፊዎች ብሽሽቅ ፣ ቀልድና ትርርብ ነበር ። ከሁሉም ከሁሉም ደስ የማይልና ጋጠወጥ ድርጊት ሲያጋጥም ታዳምያኑ በሙሉ በአንድ ድምጽ የሚያሰሟት የተቃውሞ መዝሙር መቼም ቢሆን አልረሳትም ። ትዝም ትለኛለች ። "አቤት ቆሻሻ ፣ አቤት ቆሻሻ ፣ አቤት ቆሻሻ " አቤት . . .እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወጉ ደርሶኝ ቃሊቲን በጎበኘሁ ጊዜም ይህችን "ቆሻሻ " የምትባለውን ቃል በተደጋጋሚ የሚጠሩበትን ሰዎች አይቻቸውም ነበር ። እነዚህም " ቆሻሻ " ተብለው የሚጠሩ ሰዎች በግረሰዶማዊነት ተይዘው የተፈረደባቸው ሰዎች ናቸው ።" ቆሻሾቹ " ማደሪያቸው ሽንት ቤት ፤ መዋያቸው የቆሻሻ ገንዳ ስር ነበር ። ይህን ሁኔታ መንግስት አዝዞ በወንጀላቸው እንዲቀጡ የወሰመባቸው ሳይሆን እስረኛው በራሱ ህግ አውጥቶ ድርጊቱን መፀየፉንና በኢትዮጵያም የተጠላና ሥፍራ የማይሰጠው መሆኑን ማሳየቱና ማረጋገጡም ነው ። 


እነዚህን በቃሊቲ " ቆሻሾች " ተብለው የሚጠሩትን መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ "ቀላጮች " እያለ ይጠራቸዋል ። " . . . አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ" 1ኛ ቆሮ 6፣9 ይሁንና ዓለም በተባለች በሰፊዋ ስታዲየም ዛሬ ዛሬ ደግሞ የሚገራርሙ ነውረኞችና ቆሻሻ ድርጊት ፈጻሚዎች ከሚገባው በላይ ቁጥራቸው እጅጉን ከፍ ብሎ በመታየት ላይ ነው ። በተለይ በሀገራችን በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህ አስያፊ ድርጊት እጅግ በረቀቀ መንገድ እንዲስፋፋ እየተደረገ መሆኑን ማሳያ የሚሆኑ ዋቢዎችን መጥቀስ ይቸላል ። ድርጊቱን አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በተለየ ሁኔታ ለዚህ ቆሻሻ ተግባር የሚመለምሉት ጨቅላ ህጻናትን መሆኑ ነው ። በተለይ እንደ አባት የሚታይ መምህር ለትምህርት የላካችሁትን ጨቅላ ልጃችሁን ሲጫወትበት መስማት ይዘገንናል ። ባለፈው ሰሞን አንድ መምህር ይህን ቆሻሻ ተግባር በህጻናት ልጆች ላይ ፈጽሞ በመገኘቱ በፍርድቤት የነበረውን ክርክር ላየ ድርጊቱ ወደፊት ከባድ እየሆነ ለመምጣቱ ምልክትም ነው ። የአውራ አምባው ዳዊት ከበደ በፌስቡክ ገጹ ላይ በግልጽ ይህ አስፀያፊና ቆሻሻ ተግባር በውቢቷ ሀዋሳ ከተማ በግልጽ በተከፈተ የመዝናኛ ክለብ ውስጥ ለውጭ ሀገርና ለሀገር ውስጥ ቆሻሾች ህጻናትን እንደሚቀርቡና እንደሚቸበቸቡ የክለቡን ስም ጠቅሶ መዘገቡን ስናይ በጣም ያስፈራል ። ይህ ድርጊት ሲፈጸም የአካባቢው መስተዳድር አያወቀውም ለማለት አይደፈርም ።

Monday, March 07, 2016

ደጉ ሳምራዊ

እነሆም አንድ ሕግ አዋቂ ፈሪሳዊ ኢየሱስን ሊፈትነው ተነስቶ፦ “መምህር ሆይ የዘለዓለምን መንግስት እንድወርስ ምን ላድርግ?” አለው። “እርሱም በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነባለህ?”አለው። ፈሪሳዊውም መልሶ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህም ውደድ፣ባለእንጀራህን እንደርስህ  ውደድ”አለው። ኢየሱስም “እውነት መለስህ ይህንን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ” አለው። ፈሪሳዊው ግን ራሱን ሊያጸድቅ ወዶ ነበርና ኢየሱስን “ባለንጀራየስ ማን ነው ? ” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ “አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤እነርሱም ደግሞ ገፈፉት፤ደበደቡትም፤በህይዎትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ። ድንገትም አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን ሲሄድ ወደ እርሱ መጣ አይቶትም አዘነለት፤ቀርቦትም ዘይትና የወይን ጠጅ በቁስሎቹ ላይ አፍስሶ አሰራቸው፤በራሱ አህያም ላይ አስቀምጦት ወደ እንግዶች መቀበያ ወሰደው ጠበቀውም። በማግስቱም ሁለት ዲናር አውጥቶ ለባለቤቱ ሰጠና 'ጠብቀው ከዚህም በላይ የምትከስረውን ሁሉ እኔ ስመለስ እከፍልሃለሁ' አለው። እንግዲህ ከእነዚህ ከሦስቱ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ባልንጀራ የሆነው ማንኛው ይመልሃል? ” አለው  እርሱም “ምህረት ያደረገለት”አለ። ኢየሱስም “ሂድ አንተም እንዲሁ አድርግ”አልው።

በሕይዎት ጎዳና ስንጓዝ ምን እንድሚያጋጥመን አንውቅም። ቀደም ሲል በቀረበው ታሪክ ውስጥ ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ይጓዝ የነበረው ሰው መጨረሻ አስከፊ እንደነበር አይተናል። ይህ ሰው ምን እንደሚያጋጥመው ቀደም ብሎ የተረዳ ቢሆን ኖሮ ጉዞውን በሌላ አቅጣጫ ወይም በሌላ ቀን ባደረገ ነበር። በህይወታችን ብዙ ፈተናወች ይገጥሙናል። ብዙ ጊዜ ወደፊት የሚገጥመን ነገር ምን እንደሆነ ሳናውቅ የጉዟችንን መስመር እንወስናለን። ሕይወት የእጣ ፈንታ ጉዳይ እንደመሆኗ አንዳንዴ መልካም ነገር አንዳንዴ ደግሞ ክፉ ነገር ያጋጥመናል። ምርጫችን ጥፋትን ሊያስከትልብን ይችላል፤ሞትን እስከማስከተል ድረስ። አንዲት የቤት እመቤት ከዕለታት  አንድ ቀን ያጋጠማቸውን ታሪክ እንደሚከተለው ይገልፃሉ። “ባልፈው ሳምምንት”አሉ አንድ ወጣት ልጅ የቤቴን በር አንኳኳ። በሬን ከፍቸ ስጠይቀው ስሙንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሆኑን የሚገልጽ መታወቂያ ወረቀት አውጥቶ አሳየኝ። ሥራ ፈላጊ መስሎኝ ለእርሱ የሚስማማ ሥራ እንደሌለኝ ገልጨለት መታወቂያውን ስመልስለት ሌላ ወረቀት በተጨማሪ አውጥቶ አሳየኝ። “ሥራ አይደለም  የምፈልገው የእኔ እናት እባክዎን ሊረዱኝ ይችላሉ”አለኝ። የሰጠኝን ወረቀቅት ስመለከት የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደሙ እንዳለብት አወቅሁ።


“ቀደም ሲል አንዲት የሴት ጓደኛ ነበረችኝ እናም”ብሎ ሊቀጥል ሲል አቋረጥሁትና “ይብቃህ የኔ ልጅ ሁሉንም ነገር ልትነግረኝ አያስፈልግም”አልሁት። “እባክዎ እናቴ ሰውነቴ በበሽታው እጅግ ተዳክሟል፤ሆኖም አገሬ መግባት አለብኝ ወደ አገሬ የምሄድበት ጥቂት ገንዘብ እንዲሰጡኝ እለምነዎታለሁ”አለኝ። ልጁን በጥሞና ተመለከትሁት፤ ዕድሜው ሃያወቹ ውስጥ ያለ ይመስላል፤ሰውነቱ ግን በበሽታው ተጎድቶ የደከመና የመነመነ ነው። ለጉዞው እንዲሆነው በማለት ጥቂት ገንዘብ ሰጠሁት፤እንዲሁም ምግብ አቀረብሁለት። “እግዚአብሔር ይስጥዎ በጣም አመሰግናለሁ ውለታወን መቸም አልረሳውም”ብሎኝ ሄደ። ለዓይኔ እየራቀ ሲሄድ እንባየን መቆጣጠር አልቻልሁም። “ወጣቶችን በአፍላ የምርታማነት ዘመናቸው የሚቀጭ እንዴት ያለ በሽታ ነው? የዚህ ልጅስ ህይወት ምን ትርጉም ይኖረዋል? ልጃቸውን ለትልቅ ደረጃ የተመኙት ወላጆቹስ በዚህ ሁኔታ ሲቀበሉት ምን ዓይነት ከባድ ኀዘን ይሰማቸው ይሆን?”ብዬ አዘንኩ። ይህ ወጣት ግን አንድ ፍላጎት ብቻ ያለው ይመስላል አገሩ ገብቶ መሞት።


1) እርስዎ ከላይ  በታሪኩ በተጠቀሱት በቤት እመቤቲቱ ቦታ ቢሆኑ ምን ያደርጉ ነበር?  ወጣቱን  “ዘወር በል”  ብለው ያባርሩት ነበር ወይስ እንደ ወይዘሮዋ ምግብና ገንዘብ ይሰጡት ነበር?
2) በወላጆቹ፣ በእህትና በወንድሞቹ ቦታስ ቢሆኑ ወደ ቤት ተመልሶ ሲመጣ  እንዴት ነው የሚቀበሉት?
3) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞዎት ያውቃል?
4) እርስዎ እንደ ወጣቱ ላለመሆን ምን እያደረጉ ነው?
5) ኤች አይ ቪ እያደረሰ ስላለው ችግር ያለዎት አስተሳሰብ ምንድን ነው?