Monday, February 24, 2025

ሽፍቶችና መሪዎች

መሪዎች ወይም በድንቁርና ወይም በክፋት ወይም በራስ ወዳድነት ወይም በሌላ ምክንያት የተነሳ ወደ ነጂዎች ሲለወጡ ህዝቡ መነዳት ስለሚከፋው ከውስጡ ከአንጀቱ ሽፍቶችን ያፈልቃል ፡፡ እነዚህ ሽፍቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በግልፅም ሆነ በስውር ከህዝቡ ሙሉ ድጋፍ ያገኛሉ ፡፡ ህዝቡ አቀፋቸው ይባላል ፡፡ ስለዚህም ሰነባብተው ሰውተውና ተሰውተው ያሸንፋሉ፡፡ሽፍቶች ነጂዎችን ያስወግዳሉ፡፡ እፎይ ግልግል…… ከዚያስ 

ከዚያማ ሽፍቶች የነበሩ መሪዎች ይሆናሉ- እነሱም ሰነባብተው ለገዛ ምክንያታቸው ወደ ነጂዎች እሰኪለወጡ ድረስ ፡፡ በራሺያ ሰፊ አገር እነ ሌኒን ፣እነ ትሮተስኪ ድንቅ ሽፍቶች ነበሩ፡፡የዓልም አንድ ስድስተኛ ህዝብ በሚኖርባተ በቻይና አገር የተነሱት እነ ማኦ፣ በ ጁ እና ኤን ላይ ተወዳጅ ሽፍቶች ነበሩ፡፡ በቬትናም እነ ሆ ቺ ሚን የሚያስገርሙ ሽፍቶች ነበሩ፡፡ በኩባ እነ ፊደል ካስትሮ ፣እነ ቼ ጉዌቬራ ታይተው ተሰምተው የማይታወቁ፣ዓለምን የነሸጡ ሽፍቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ቆንጅዬ ሽፍቶች የህዝብን ብሶት ይዘው ስለተነሱ ድል አደረጉ፡፡ በሽፍትነታቸው ዘመን ተዓምር ነው ወይም ምትሃት ነው የሚያሰኝ ብዙ ጀብዱ ፈፀሙ ፡፡ የሽፍትነታቸው ዘመን ሲተረክና ሲፃፍ ገድል ይመሰስላል ፡፡ ገድል ነው ደግሞ -ምድራዊ ሆነ እንጅ ፡፡

እንደተለመደው አገርን በሴት ብንመስላት ፣ሽፍቶች የነበሩት ተለውጠው መሪዎች ሲሆኑ ውሽማ የነበረው ሰውዬ ባል ሆነ እንደ ማለት ነው፡፡ሰውየው ያው ሆኖም ፣ በውሽምነቱ ሌላ በባልነቱ ሌላ ፡፡ አረ የትና የት

ባጠቃላይ እንዴው በጭፍን ያህል ስንናገር በአንድ ልብ በአንድ ወኔ ለአንድ ዓላማ ሲዋጉ የነበሩት ሽፍቶች ፣መሪዎች በሆኑ በማግስቱ አላማቸውም ልባቸውም መለያየት ይጀምራል ፡፡ ልዩነቶቻቸው እየበዙ እየከረሩ ሲሄዱ ፣ ጠላትነት እየተንፏቀቀ መሃላቸው ይገባል፡፡በራሺያ ስታሊን ትሮትስኪን ካገር ያባርረዋል ፡፡ከዚያም ሜክሲኮ ድረስ ልኮ ያስገድለዋል ፡፡ሽፍቶች የነበሩት የትሮትስኪ ወገኖች ፣ ሽፍቶች በነበሩት በስታሊን ወገኖች ይጨፈጨፋሉ፡፡

በቻይና ሽፍታ የነበረው ሊዮ ሻዎ ቺ፣ሽፍቶች ወደ መሪዎቹ ሲለወጡ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ ቆዬ፡፡ ያውም አሪፍ! ተዘርዝሮ የማያልቅ አደጋ አብረው ያሳለፉና ስንትና ስንት ድል አብረው የተቀዳጀጁ ነበሩ ማኦ እና ሊዮ፡፡ በሽፍትነት ዘመን በደጉ ዘመን ፡፡ አለፈቻ የሽፍትነት ዘመን፡፡ አይ ደግ ዘመን ስንትና ስንት አመት የመሞት የመቁሰል አደጋ እያለበትም፣ ረሀብና ውሀ ጥም እየተጠናወተውም አብረን ነበር እምንቆስለው፣ እምንሞተው፣ ባንድ ላይ ነበር እምንራበው ፣እምንጠማው ፣ስናገኝም አብረን ነበር እምንደሰተው ፣ ያውም አንተ ቅደም አንተ ቅደም እየተባባልን፡፡ አይ ውቢቱ የሽፍትነት ዘመን ሁላችንም የህዝባችን ኡኡታ ጠርቶን ወጣን ከየቤታችን ፡፡ ተዋጋነው ያን ኡኡ ያሰኘው የነበረውን (እኛም ህዝብ ነንና የህዝባችን ያካሉ ቁራጭ ነንና የህዝባችንም ኡኡታ ውስጣችንም ነበረ) እና ባንድነት ተዋጋነው -ያኔ ቢያስፈልግ አንተ ለኔ ትሞትልኝ ነበር ፣እኔም ላንተ፡፡ 

ዛሬ ግን ዞረን እኔና አንተ እርስ በርሳችን ልንጋደል ሆነ…በመሀሉ ምን መጣና እንዲሀ ለወጠን? እኔም አንተም እያወቅነው!? ተጋግዘን ጭራቁን ማባረር ሌላ፣ተጋግዘን ቻይናን መምራት ሌላ፡፡ የት ነው የተጠፋፋነው መሰለህ? ሁለታችንም ለቻይና ህዝብ ለመሞት ወይም ለማሸነፍ ወጣን፡፡ በለስ ቀናን አሸነፍን ፡፡ ቀጥሎ ምን መጣ? ያቺን ከህይወታችን አብልጠን እየወደድናት እኩል ልንሞትላት ተስማምተን የተዋጋንላት -ቻይና፡፡

አሁን ተራችን መጣ ፣እንምራት እናታችንን ስንል እኔ በዚህ በኩል ይሻላል ስል አንተ በዚያ በኩል ይሸላል ስትል መንገዳችን ተቃራኒ ሆነ ፡፡ አንተም ከልብህ ካንጀትህ ለቻይናችን ይበጃታል ያልከው -ወደዚያ አመራ፡፡ እኔም ከልቤ ካንጀቴ ለህዝባችን ይሻለዋል ያልሁት ወደዚህ አመራ፡፡ የኔ እና የአንተ አብሮ መጓዝ አበቃ ።

እየወደድኩህ እያከበርኩህም ያንተ መንገድ  ቻይናን ይጎዳታል እንጅ አይበጃትም በዬ ስላመንኩ እቃወማለሁ፡፡ አንተም እንደዚህ ነው ስለእኔና ስለቻይና የምታስበው ፡፡ ምነው ያንተ መንገድ ትክክል በመሰለኝና አብሬህ በተጓዝኩ ባይሆንልኝም ያንተንና የቻይናን መንገድ ለመጥረግ በሞከርኩ፡፡ግን ባንተ ቤት የኔ መንገድ የቻይና ጥፋት በኔ ቤት ያንተ መንገድ የቻይና ጥፋት ፡፡

ቻይና ከመጥፋቷ በፊት ማንም ግለሰብ መጥፋት አለበት- አንተም ሆንክ እኔ፡፡አያሳዝንም?  ወይ እኔ ወይ አንተ መጥፋት ሲኖርብን? እኔና አንተ ልንቻቻል አልቻልንማ! ምናልባት ላንጠፋፋ እንችል ነበር ይሆን? ከኛ በኋላ የሚመጡ አብዮታውያን ያስቡበት፡፡የት እንደተጠፋፋን መርምረው ይደረሱበት፣እዚያ ሲደርሱ እንደኛ እንዳይጠፉ፡፡  

በታሪክ የምናውቃቸው ሊዮ፣ሻዎ፣ቼ እና ማኦ እስከመጋደል ደረሱ ፡፡ ቼ እና ካስትሮ እንደተከባበሩ እንደተዋደዱ ተለያዩ፡፡በታሪክ ሳይሆን በምናባችን ቼ እንዲህ ብሎ ያስባል፡፡በዚህ በኩል ቀድመው ለህዝባቸው የታገሉና ታግለው አሸንፈው በኋላ ‹ቀኝ ኋላ ዙር› ብለው እርስ በርስ የተፋጠጡ አሉ፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የመላው ዓለም ጭቁኖች ብዙ ናቸው ፡፡ የኩባ ህዝብ ትንሽ ነው ፡፡ እናም ነፃ ወጥቷል፡፡ 

በሚቀጥለው ምእራፍ እኔና ፊደል እርስ በርስ መጠራጠር ፣መጠንቀቅ ፣መጠማመድ ፣መገዳደል ከመሚኖርብን ቀድሜ ውልቅ አልለውም? ነፃነት የጠማው ህዝብ መች ጠፋና ሰው እንደሆነ ያው ሰው ነው ፡፡ የትም ቢኖር ምንም ዓይነት መልክ ቢኖረው ፣ ምንም አይነት እምነት ቢኖረው፡፡ ስለዚህ ወደ ቦሊቪያ!

ምናብ ምን ይሳናታል? አሁን ደሞ ፊደል ካስትሮን እንሆናለን ፡፡ በምናብ ፀጋ ያስባል ፡፡ ፊደል ፡፡ ያየዋል ‹ቼ› የጤና ጥበቃ ሚኒስትርም ሆኖ ኩባን ሲመራ ፣የኢንዱስትርም ሆኖ ሲያገለግል፡፡

ገና ይህ ሰውዬ እዚህ ከመምጣቱ በፊት ፣እኛን ነፃ ከማውጣቱ በፊት ፣ በሦስት ሌላ አገር ውስጥ ተዋግቷል ፡፡ አስማውን በአንድ እጁ እያስታመመ ፣ጠላት ላይ በሌላ እጁ እየተኮሰ ፣ ተኩሱ ጋብ ሲል ቁስለኞችን እያከመ፡፡ ያን ሁሉ ጀብዱና ከሞት መፋጠጥ ለምዶ አሁን ኩባን ለማስተዳደር ይቸከዋል፣ይሰለቸዋል፡፡ ምን በወጣው!

በል እንግዲህ ቼ ቢሮክራሲውና ወረቀቱ በቃህ ፡፡ ከእንግዲህ እኛ እንቀጥላለን ፡፡ሂድና ደሞ ሌላ ኩባ ውስጥ ገብተህ ተዋጋ፡፡ ተዋጊ ነህ አስምን በየደቂቃው ትዋጋለህ ብቻህን ምነው አንዲቷን እንኳ በአስም መታፈን እኔ ልታመምልህ በቻልኩ፡፡ሂድ በቃ ተዋጋው ሰይጣንን፡፡ይቅናህ የኔ ጎበዝ ይለውና ይሰነባበታሉ፡፡

ይህ በኩባ ሆነ ፡፡ ወደ ቻይና ስንመለስ ግን ማኦ እና ሊዮ ሻዎ ቺ ተቃቅረው እናገኛቸዋለን ፡፡ነገሮች እየተባባሱ ይሄዳሉ፡፡ አንድ ቀን ሊዮ ሻዎ ቺ ካገር ለመጥፋት በአውሮፕላን ሲበር የሊቀመንበር ማኦ ወገኖች ነቅተውበት ኖሮ ተኩሰው አውሮፕላኑን አጋይተው ይገድሉታል ፡፡ ዘመናት ካለፉ በኋላ  ደግሞ እነ ዴንግ ሲያዎ ፒንግ የሊቀመንበር ማኦን ሚስትና ሦስት ግብረ አበሮቿን ‹‹አራቱ ወንበዴዎች››(ጋንግ ኦቭ ፎር ) በይፋና በብዙ ልፈፋ አዋርደው ያቀርቧቸዋል፡፡

መንግስት በአንድ መልኩ የህዝቡ ጠባቂ ነው ፡፡ ከውጭ ጠላት ይጠብቀዋል፣ እርስ በርሱ እንዳይባላም ይጠብቀዋል፡፡ በሌላ መልኩ ግን መንግስት ምንም ያክል ጥሩ መንግስት ቢሆን አስገዳጅ ኃይል ነው፡፡ለዚህም ፖሊሶች፣ ፍርድ ቤቶች ፣እስር ቤቶች ምስክር ናቸው ፡፡ስለዚህ አንዳንድ ሽፍቶች አሉ፣ ከሽፍትነት በኋላ መሪነቱ የማይጥማቸው ፡፡ከነዚህ እጅግ ዝነኛውና የመላ ዓለም ተራማጆች የሚያመልኩት ጀግናው ቼ ጉዌቬራ ነው ቪቫ ቼ!

ቼ የአብዮታወያን አርአያ ነው ፡፡

‹‹ሀ›› ብልን ስንጀምር የኩባን  ሽፍቶች ወደ ድል ከመሯቸው ቀንደኛ ተዋጊዎች አንዱ የሆነው ቼ ጉዌቬራ ኩባዊ አይደለም ፡፡የአርጅንቲና ሰው ነው፡፡ ‹‹ለ›› ብለን ስንቀጥል ቼ ጉዌቬራ በኩባ ከመከሰቱ በፊት በሦስት ሌሎች የላቲን አሜሪካ አገሮች ውስጥ ከጭቁን ወታደሮች ጋር የተፋፋመ የሽምቅ ዊጊያ ተዋግቷል ፡፡ ኩባ አራተኛ አገሩ ናት ፡፡ በመጨረሻም ኢምፔሪያሊዝምን እየተዋጋ በጀግንነት የወደቀው በአምስተኛ አገሩ በቦሊቪያ ነው ፡፡

ቼ ጉዌቬራ የአብዮታውያን አብዮተዊ ነው ልንል እንችላለን ፡፡አባዛኞቹ አብዮታውያን በትውልድ አገራቸው ውስጥ የገዛ ህዝባቸውን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት ነው ሚዋጉት ፡፡ ቼ ግን ሌላ ነው ፡፡የሰውን ልጆች ከጭቆና ለማላቀቅ ነው፡፡ የትም ይሁን የትም ጭቆናን እንዋጋለን! ማንም ይሁን ማንም ጨቋኝን እናወድማለን! ማንም ይሁን ማንም ለጭቁን እንሞታለን!

ቼ ጉዌቬራ አስም ወይም አስማ የሚባለው ትንፋሽን እፍን እፍን የሚያደርገው ፣በሽተኛውን አስጨናቂና የሚያይ የሚሰማውን  ሰው የሚያሳቅቅ በሽታ ፣ ገና በልጅነቱ ተቆራኘው ፡፡በሽታው ከማየሉ የተነሳ ቼ ትምህርት ቤት መግባት አልቻለም ፡፡አስተማሪ ቤቱ እየመጣ ያስተምረው ነበር ፡፡ እንግዲህ ቼ ጉዌቬራ ግማሽ የአልጋ ቁራኛ ፣ግመሽ የቤት እስረኛ ሆኖ ነበር መኖር ያለበት እንጅ ፣ጦር ሜዳ ይሄዳል ብሎ ማን ያስብ ነበር ?

እንግዲያው ምን ለውጥ መጣ? በሽታው ተሻለውን? በጭራሽ ቼ ከበሽታው ጋር እልክ ተያያዘ፡፡ያመኛል እሰቃያለሁ እንጅ በሽተኛ አይደለሁም ፡፡እምቢ በቃ ! በመንፈስ ጥንካሬ ብዛት ነው ቼ ህክምናም የተማረው ፣ጭቆና ላይም የዘመተው ፡፡ አስቸገረ ቼ ጉዌቬራ ላቲን አሜሪካን አመሳት ፡፡ የጭቆናና የብዝበዛ አማልእክትን እንቅልፍ ነሳቸው፡፡ 

ሲ አይ ኤ ተላከ፡፡ቼን በቦሊቪያ ጫካ ከበቡት ፣ገደሉት መልእክታቸው ተሳካ ግን-ቼ ጉዌቬራን ገደልነው ብለው ቢያወሩ ፣ ማንም አያምናቸውም ፡፡ማንም፡፡ ስለዚህ የሬሳውን ፎቶግራፍ አሰራጩ፡፡‹‹ቼ ጉዌቬራ ቅዱስ ነው ››የሚሉ አሉ ባለጥይቱ ቅዱስ ፡፡ እንግዲህ የቼ ጉዌቬራ አምላክ የነፃነት አምላክ አብሮን ይሁን ፡፡ አሜን ፡፡