Wednesday, July 11, 2018

የጋብቻ ጥያቄ

ቀን 3/11/2010 ዓ.ም
ለፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ
አስመራ


                 ጉዳዩ፦ የጋብቻ ጥያቄን ይመለከታል
እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን በኢኮኖሚ፣ በባህል፣ በጋብቻ የተሳሰረ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለን
ህዝቦች ነን። ከዓመታት በፊት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት ወይም አለመግባባት የብዙ ወጣቶችን ህይወት
የቀጠፈና ደም ያፋሰሰ እንዲሁም ሁለቱን ህዝቦች ፊት ያዟዟረ ቢሆንም፤ በቅርቡ የተጀመረው ጥላቻን በምህረትና በይቅርታ
የመሻር ሂደት ሁላችንንም የደስታ እንባ አስነብቶናል። እኔም ዶ/ር ጌታነህ ካሴ የተባልሁት ግለሰብ በጅማ ዩኒቨርሲቲ
የህክምና ማዕከል የመጨረሻ ዓመት የህክምና ተማሪ ስሆን በክቡር ዶ/ር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዓብይ አህመድ የተጀመረውንና
በሃገር አቀፍ ደረጃ ጎልቶ በመታየት ላይ ያለውን የሰላም፣የፍቅርና የመደመር መርህ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት
የበለጠ ለማጠንከር ሁለቱን ህዝቦች ልብለልብ ለማስተሳሰር ክቡርነትዎ የጋብቻ ጥያቄዬን ተቀብለው አንዲት ውብ ሰሜናዊት
ኮከብ ጽብቅቲ ዓይናማ ሹርቤ ቆንጆ ልጃገረድ ይሰጡኝ ዘንድ በትህትና እጠቃለሁ።
ከሰላምታ ጋር
              ዶ/ር ጌታነህ ካሴ(MI)
       ጅማ ኢትዮጵያ

ግልባጭ
ለኤርትራውያን ልጃገረዶች በሙሉ

Monday, July 09, 2018

ቅኔ ነሽ

የጠገበው ሲሄድ የራበው ሲመጣ
ሲስተር አ'ዘነጋሽ ምጣድሽ አይውጣ
የሚል ግጥም ልፅፍ ልቀኝ ያመረኝና
ቃላት አቅም አጥተው ይሆናሉ መና
የማምዬን ናፍቆት ፍቅርሽ የሚያስረሳ
ለቁርስ የጋገርሽው የሚተርፍ ለምሳ
በፈተና ብዛት ትጥቅሽ ያልተፈታ
የጠላትን ጉራ ትዕግስትሽ የረታ
የሥጋ ፍላጎት ደፍሮ ያልፈተነሽ
ረሃብ ውኃ ጥም ያላመነመነሽ
ወርቅሽ ያልተፈታ አንች እኮ ቅኔ ነሽ
ታችቤት : ሰኔ 30 /2010 ዓ.ም
 እንኳን ደስ ያለሽ ለማለት ያህል

ልቤን አታድርቀው

ግድፈት የሌለበት እውነት መናገሬን ልብህ እያወቀው፣
እገሊት ከፍቷታል ያ ጎረምሳ ዝቷል በሚል እንቶ ፈንቶ ልቤን አታድርቀው።
አንተን ብሎ ትሁት ገልጋይ ደም አድራቂ፣
አንችን ብሎ ሸምጋይ ድንቄም አስታራቂ፣
ፍቅር ያሸንፋል በሚል የምፀት ቃል ከምትሳለቂ፣
ተመሳስሎ ኗሪ የቀበሮ ጃኬት ካፖርትሽን አውልቂ ።
እውነቱን ተናግረሽ ስትሄጅ ቢመሸብሽ ከዛፍ ስር እደሪ፣
ከትንሹ እግዚአብሔር ከህሌናሽ ጋራ በሰላምሽ ኑሪ።
ከራድዮን 28/10/2010 ዓ.ም

ረቢ

ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ!
መምህር ሆይ
ይህን ሁሉ ዘመን ደብተር ተሸክሜ፣
ዘመኔን ቆንጥሬ እድሜየን ዘግኜ፣
ቀኔን አባክኜ ከፊትህ ታድሜ፣
ሌጣ አዕምሮዬን ለፍርጃ ሰጥቸህ፣
በገማ ቴዎረም በበሰበሰ ቃል ሞልተኸኝ ሰለቸህ።
በዚህ ሁሉ ዘመን
እድሌ ተስፋዬ ባንተ መዳፍ ወድቃ፣
አንተን በማዳመጥ ነፍሴ ማቃ ማቃ፣
የዛሬ እልፍ ዓመት በወጣ መረጃ፣
እውቀቴ ብቃቴ ባንተ ተፈርጃ፣
ይህን ሁሉ ዘመን
አንተ እኔን ብቻ ስትፈትን ስትለካ ፣ስትፈትን ስትለካ፣
የመንገዴ አቅኚ የጨለማዬ ጦር እያልኩህ ስመካ፣
ውሉ ሲመረመር የሆንህበት ምስጢር የህይወቴ ሳንካ፣
ወድቀሃል ያልኸኝ ለት፣ ሚዛንህ ሚዛኔ ሰባራ ነው ለካ።
ቀድሞስ አንስታይን መች ባንተ ተለካ!
ራስህን ስፈር፣ ራስህን መርምር፣ ራስህን ለካ።
ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ!
እኔን ብሎ ሰሚ አንተን ብሎ ብርሃን ድንቄም መምህር እቴ!
ይህን ሁሉ ዘመን እድሜዬን ቀንጥሼ እኔን በመስጠቴ፣
ደንቆሮ ስትለኝ አንተን አይጨምርም እስኪ እንደው በሞቴ?
ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ!
እነ ዛራ’ስቱራ፣ እነ ክሪሽና
ሶቅራጥስ፣ፕሉቶ፣ እየሱስ ክርስቶስ ባለፉበት መንገድ፣
የምትንገዳገድ የምትወላገድ፣
ትውልድ የምትገድል በቅምጥ “ጀኖሳይድ”
ሆላ መምህር ሆላ፣ሆላ ረቢ ሆላ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ።
ይህን ሁሉ ዘመን አድምጨህ አድምጨህ
ተስፋየ ካጨጨ ካጣሁ አንድም መላ፣
ወድቀሀል ብለሀል መቼስ አታስፈጨኝ ከእንግዲህ በኋላ።
ሆላ መምህር ሆላ፣ ሆላ ረቢ ሆላ፣
እየሱስ ክርስቶስ በተጠራበት ስም የተጠራህ ሁላ።
አርባ ‘ምስት ደቂቃ አርባ ‘ምስት ደቂቃ፣
እየተሰፈረች እድሜዬ ተሰረቃ፣
አስተምረኝ ብዬ ራሴን ሰጥቸው ነዝንዞኝ ሲያበቃ፣
ደግሞ ሌላ ነዝናዥ ጠመኔውን ይዞ ሲያስረኝ በፈረቃ፣
እንዲህ እንዲህ ተብላ ዘመኔ ተፍቃ፣
ሰሌዳ ሆኛለሁ ከእንቅልፌ ስነቃ።
ራሴን አገኘሁ ሆኘ ሰባራ እቃ።
መምህር እሽሩሩ፣
መምህር እሽሩሩ፣
ውረድ ከጀርባዬ እንግዲህ ይበቃል፣
ራሱን አስተምሮ አንስታይን ይነቃል።
ምንጭ፦ የቀንድ አውጣ ኑሮ በይስማዕከ ወርቁ