Thursday, August 17, 2017

ሳይኮፓትስ

ለጋራ ደህንነት የማይጨነቁ
ጤነኛ ነን ሲሉ ታመው የማቀቁ
ላያቸው  ያማረ  ልስን መቃብሮች
በበግ ለምድ ያጌጡ አስመሳይ ቀበሮች
አጉራ ዘለል ወይፈን ተራጋጭ ጊደሮች
ጋውን የለበሱ የተቋም አውሬዎች
ጊዜ ያለፈበት ክኒን ቸርቻሪዎች
ከአምላክ የተጣሉ አሉ ወንበዴዎች
ሐኪሞች ሲባሉ የመርዝ ነጋዴዎች
ባለጌ መች አጣን አሉን ጋጠ ወጦች
በልተው የማይጠግቡ የሆስፒታል አይጦች
መርዛቸው  የማይለቅ ተናዳፊ ጊንጦች
ወንጀል በዞረበት ቦታ ማይታጡ
እጅ ከፍንጅ ተይዘው የማይደነግጡ
ላደጉበት ባህል እውቅና ማይሰጡ
ለምድራዊ ሥልጣን የማይታዘዙ
ለፈጣሪያቸው ህግ ፍጹም ማይገዙ
በዓይነ ስውር ፎቶ ዶላር ሚበደሩ
የድሃ አደጉን ልጅ ጾም የሚያሳድሩ
ከረዥም ልምዳቸው እውቀት ማይቀምሩ
አሊያም ከደጋጎች አንዳች ማይማሩ
በዝባዦች ሞልተዋል በየጉራንጉሩ
ውስጣቸው ሲገለጥ እጅግ ሚከረፉ
ከአጋንንት አለቆች በግብር የከፉ
ከሙዳዬ ምፅዋት ቅኔ የሚዘርፉ
ደግ ቅን አሳቢ ጤነኛ ሚመስሉ
አትሮኖስ ላይ ቆመው መንፈስ ሚያታልሉ
መዝሙር ሲያልቅባቸው ቀረርቶ ሚሞሉ
በበትረ ሙሴ አምሳል ለአንገት ሰይፍ ሚስሉ
ከቤተ መንግስትም ከቤተ መቅደስም ሳይኮፓቶች አሉ


Note: Psychopaths are individuals with Antisocial personality disorder and they are characterized by Continuous disregard for the safety of oneself and others, Violation of the rights of others without feeling remorse, Failure to learn from experience, Social deviance, Manipulative or parasitic attitude and Resistance to authorities. They often wear ‘a mask of sanity' and may appear quite normal, charming, and understanding. Surprisingly there are three and half times more psychopaths in senior executive positions than there are in the general population.
©ጌች ቀጭኑ ነሐሴ 11/2009 ዓ.

Tuesday, August 08, 2017

እይታ

ከሁሉ አስቀድሜ በዚች አጭር ጽሑፍ ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ የማስበውን ሀሳብ ለማስተላለፍ  እንጅ አንዱን አሳንሶ ሌላውን ከፍ የማድረግ ዓላማ እንደሌለኝ ለመግለጽ እወዳለሁ። ምናልባት መስሎ የሚታየው ካለ ግን እርሱ አስተሳስቡን ያስተካክል።

ያ ስሙን የማላስታውሰው መዝገበ ቃላት “ስብሰባ የሚለው ቃል በቁሙ ሲፈታ  ውኃ ውኃ የሚሉ ሰዎች ተመራርጠው የሚሰባሰቡበት፤ በየደቂቃው አፋቸውን በሀይላንድ ውኃ እየተጉመጣመጡ ውኃ የማያነሳ ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩበት ፤ በመጨረሻም ከውኃ የቀጠነ ውሳኔ አሳልፈው የሚለያዩበት የሰዎች ጥርቅም ነው ” ያለው እውነቱን ሳይሆን አልቀረም። እንደዚህ የምለው ያለ ምክንያት አይደለም፤ ላለፉት አራት ዓመታት እንዳስተዋልሁት  ክረምት  በመጣ ቁጥር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተባለ የተለያዩ ስብሰባዎች (ስልጠናዎች)ተዘጋጅተዋል ተካሂደዋልም። አንዳቸውም ግን የህክምና ተማሪዎችን  አሳትፈው አያውቁም ። ከ“ጥልቅ ተሐድሶ”ው በስተቀር።

“ይህ የሆነው የህክምና ተማሪዎች ጊዜ ስሌላቸው ነው።” ብሎ የሚከራከር የዋህ ይኖር ይሆናል። እኔ ግን አይመስለኝም። የስብሰባው አስፈላጊነት ከታመነበት በስብሰባው መሳተፍ ያለባቸው ጊዜ ተትረፍርፎባቸው “ክረምቱን በምን እናሳልፈው” የሚሉት ሳይሆኑ ጊዚያቸውን አጣበው የሚጠቀሙት ናቸው። ምክንያቱም በትርፍ ጊዜው የሚሰበሰብ ሰው ሃሳብ  የሚሰጠውም  ውሳኔ  የሚወስነውም ትርፍ ጊዜ  ስላለው እንጅ አስፈላጊነቱን አምኖበትና ከልቡ አስቦበት ነው ለማለት ይከብደኛል።

በመሰረቱ ለአንዲት ሀገር እድገት የሚያስፈልገው ሥራ ነው እንጅ ስብሰባ ነው ብዬ አላምንም። የግድ ስብሰባ ያስፈልጋል ከተባለ ግን  በ12ኛ ክፍል ፈተና የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ህክምና  ትምህርት ቤት የገቡ ተማሪዎችን ማሳተፍ አማራጭ የሌለው ግዴታ ይመስለኛል።“ከተባለ ወዲያ እናርገው በፍቅር ጥርስዎን ያውሱኝ ድንቸ ቆሞ አይቅር” እንዲሉ አያቴ ። እውነት ችግሩ የጊዜ ማነስ ከሆነ ሁለት ሳምንት የሚፈጀውን ስልጠና አጠር መጠን አድርጎ በአራት ወይም በአምስ ቀናት መጨረስ  ያማይቻል ሆኖ ነው? ከህክምና ተማሪ ጭንቅላት የሚመነጨውን ሃሳብ መረዳት የሚችል፣ የሚጠይቁትንም   ጥያቄ የመመልስ አቅሙ ያለው የስብሰባ መሪ ከተገኘ ማለቴ ነው።

መቼም እየተደረገ እንዳለው የAnesthesia ተማሪዎች የ”medicine” ተማሪዎችን ወክለው ይወስኑ ብሎ የሚሟገት ይኖራል ብዬ አላስብም።

©ጌች ቀጭኑ ነሐሴ 2/2009 .

Saturday, August 05, 2017

ችግር ሲደራርብ

አንዳንዴ  ችግሮች ሁሉ በሰው ላይ ያድማሉ። የመጀመሪያው ችግር ያስከተለው ሃዘንና መከራ ከልብ ሳጠፋ ሁለተኛው ይከተላል። መከራ መከራን እየመዘዘ በመሳሳብ የተቀባዩን  አሳርና ፍዳ ያበዛዋል። ጊዜና ምክንያት ተረዳድተው የችግር ሰንሰለት፣የመከራ ቀለበት  ይፈጥራሉ። በሰንሰለቱ የታሰረ በቀለበቱ የታጠረ እዬዬን ዘፈኑ አድርጎ ብሶትና ትካዜን ሲያንጎራጉር ተስፋ ቆርጦ ተስፋን  እያበቀለ ጊዜ ያመጣበትን  ጊዜ እስኪያስረሳው አካል መንፈሱ ይንገላታል። አንዳንዱ ሃዘንና ችግሩን አፍ አውጥቶ ለሌላው በማካፈል አልቅሶ ይለቀስለታል፤አዝኖ ይታዘንለታል። ያም ብቻ ሳይሆን ከከንፈር መምጠጥ አንስቶ እስከ ከባድና ውስብስብ ደረጃ ያለ እርዳታና መፍትሄ ሁሉ ይለገሰዋል። እናም ትንሽ ሲነካ ብዙ በመጮህ ችግሩ ሳይጎዳው በፊት የቅርብ የሩቅ ወዳጁን አስቸግሮ በእንጭጩ ይቀጨዋል። አንዳንዱ ደግሞ ለዚህ አልታደለም። ችግሩን ለብቻው አፍኖ በመያዝ ወደ ውስጡ እያነባ መንፈሱን በጭነንቀት እያደቀቀ አካሉን በጥያቄ እስኪያስገምት ይብሰከሰካል። ብዙ ጊዜ ሐሳብና ችግራቸውን ለብቻቸው ይዘው የሚብሰለሰሉ ሰዎች አካባቢያቸውን በስጋት የሚመለከቱ ናቸው ። ፍርሃትና ጥርጣሬ አይለያቸውም ። እምነታቸው በራሳቸው ላይ ብቻ በመሆኑም ችግራቸውን በውስጣቸው አምቀው በይሉኝታ፣በእልህና በመግደርደር  አጽናኝ ረዳት ሳያገኙ ጉዳታቸው እያየለና እየከፋ በመሄድ በእነሱ ፍላጎት ሳይሆን በችግራቸው ከአቅም በላይ መሆን ይጋለጣሉ። ነገር ግን ከረፈደ ነውና ከዘመድ ወዳጅ ሊያገኙ የሚችሉት እርዳታ ችግራቸው የሚወገድበትን ሳይሆን ችግራቸውን አምነው የሚቀበሉበትን ምክርና መፍትሔ ነው። ይህ ጽሑፍ ገመና የተሰኘ ረዥም ልብወለድ ሳነብ ያገኘሁትና በማስታወሻ ደብተሬ ከትቤ ያስቀመጥሁት ሲሆን በዛሬው እለት አንዲት የፌስቡክ ጓደኛዬ “ዛሬ ባጣም ክፍት ብሎኛል“ ብላ ፖስት ስታደርግ ከጠቀማት ብዬ ልኬላት በጣም እንደወደደችው ስለገለጸችልኝ በጦማሬ ላይ ላሰፍረው ተገድጃለሁ።ጥሎብኝ ሴት ልጅ ስትከፋ ማዬት አልወድም።
 ያለ ጭንቅ አይወጣም የሴት ልጅ ገንዘቧ፣
በከፈለች ማግስት ይቀጥናል ወገቧ፤
እያልሁኝ እሟገት እከራከር ነበር፣
መሆኗ ሳይገባኝ የልግስና በር።
ጌች ቀጭኑ!

Friday, August 04, 2017

እንጨት ሽበት

በስቴቶስኮፑ ላይ  ዝናውን ደርቦ፣
ዶክተሩ ብቅ ሲል ስድብን ተርቦ፣
ነጭ ላብ  ሲያመነጭ ተሜ ከግንባሩ፣
ዋርዱም ይጨነቃል ይቆማል ባንድ እግሩ።
አሁን በቀደምለት !
ምሁር ከኔ በላይ አዋቂነት ላሳር፣
ነው ብሎ የሚያምን ከንቱ ነው ስንክሳር፤
ዝም በል አትንጣጣ እንደ ተልባ ቆሎ፣
ስትጠየቅ ብቻ መልስ ስጥ በቶሎ።
በሽታውን ካወቅህ መድኃኒቱን አምጣ፣
የማትችል ከሆነ አማራጭ ምታጣ፣
በመስኮት  ልጣልህ ወይም በበር ውጣ፣
አንች ደግሞ ዝፍዝፍ ምን ተዘርግፈሻል፣
ስታጨሽ ስትቅሚ ቀን ነግቶ ይመሻል፤
ሀገርሽ ወዴት ነው ትመስያለሽ ጭቁን፣
ለካስ ወሎዬ ነሽ የተቋቋምሽ ድርቁን።
አንተን ደግሞ አለት ራስ ተስፋህ የጨለመ፣
አስተምሮ ሰው ሊያረግ ማን ለምን  አለመ?
አድረህ ላትሻሻል በከንቱ ደከመ።
ገዳይ የለም እንጅ ሟችማ መች ጠፋ፣
ድንቁርናም በዛ ባዶነት ተስፋፋ።
እያለ ሲዘልፈን ሲሰድበን ሲቆጣን፣
ቁም ቅምጥ ሲነሳ መድረሻ ሲያሳጣን፤
አባቱን ሊጠይቅ የመጣ አንድ ጎልማሳ፣
እንዲህ ሲል ተቀኘ ብዕሩን አነሳ፣
አወይ እንጨት ሽበት አጉል ሽምግልና፣
ለማንም የማይበጅ ከንቱ ፍልስፍና፣
ጥበብ በፀጋ እንጅ መች በእድሜ ሆነና።

ጌች ቀጭኑ ከ“ward” መልስ ሐምሌ 25/2009 .