የሐበሻ ቀጠሮ ሲባል ግን አይገርማችሁም? በፈረንጅኛ እንማራለን በፈረንጅኛ እናስተምራለን፣በፈረንጅኛ እንታመማለን፣ በፈረንጅኛ ታክመን በፈረንጅኛ እንድናለን። በፈረንጅኛ እንመርቃለን(እናመሰግናለን)፣በፈረንጅኛ እንሳደባለን። በቢዮንሴ እና በሻኪራ ዘፈን እንጨፍራለን፤ የፈረንጅ ልብስ እንለብሳለን፤ የፈረንጅ መጠጥ እንጠጣለን፤የፈረንጅ ምግብ እንመገባለን (ለማለት ቢከብድም)። ከፈረንጅ ያልወረስነው ነገር ምን አለ? እንደ እኔ ከፈረንጅ ያልኮረጅነው ነገር ቢኖር የቀጠሮ አከባበራቸውን ብቻ ነው። ፈረንጆች የሚሆኑትን ሁሉ እንሆናለን። የሚያደርጉትንም እንደ አቅማችን ለማድረግ እንጥራለን። የሰዓት አጠቃቀማቸውን ለመስረቅ ሙከራ ሲያደርግ የተያዘ ወንጀለኛ ግን ያለ አይመስለኝም።ይልቁንም ደካማ የጊዜ አጠቃቀማችንን የሐበሻ ቀጠሮ የሚል ሽፋን እንሰጠዋለን።
የሐበሻ ቀሚስ ከተነደፈ ጥጥ ይሸመን ከታኘከ ማስቲካ ይሰራ የማያውቁት ሴቶቻችን እንኳን ዳሌያቸውን ከጉልበቱ ላይ በተቀደደ የቻይና ጅንስ ወጥረው ለምን የቀጠሮ ሰዓት እንዳላከበሩ ሲጠየቁ “ምን ይደረግ የሐበሻ ቀጠሮ አይደል” ማለት ይቀናቸዋል። ወይ ሐበሻ እቴ ድንቄም ሀበሻ! የማር ሰፈፍ የመሰለ እንጀራ ጋገሮና በቅምጥ የሚስቀር ጠላ ጠምቆ ነበር እንጅ ሐበሻነትን ማስመስከር። “ትርክርክ” አለች አክስቴ። በነገራችን ላይ እኔ እስከማድግ ድረስ ሴቶቻችን በዚህ ከቀጠሉና ለቀጠሮ ያላቸው አመለካከት ካልተስተካከለ ቆሞ ቀር እባላለሁ እንጅ ሚስት የምትባል ጉድ ላለማግባት ቁርጥ ያለ ውሳኔ ላይ ደርሻለሁ። በቃ አዱኛ አበባዬን ሳላይ ብሞት ይሻለኛል።(የመጀመሪያ ሚስቴን ልፈታት ስላሰብሁ ከተሳከልኝ ማለቴ ነው) ። ቀጠሮ የማታከብር ሴት ቱ... ሞቻለኋ!
ምን ለማለት ፈልጌ ነበር ? ባለፈው ቅዳሜ እለት የሆነች ስልጠና ቢጤ ለመሳተፍ ከጥዋቱ 2:00 ላይ የሆነ ቦታ ተገኝቸ ነበር። ስልጠናው ወይም ስብሰባው በማስታወቂያ ከተገለፀው ሰዓት 80 ደቂቃዎችን ብቻ ዘግይቶ ተጀመረ። ወደ ስብሰባው አዳራሽ በጓሮ በር ገብተን እንደተቀመጥን ግማሽ ሌትር የሀይላድ ውኃ በነፍስ ወከፍ ታደለን። (እኔም እንደሰው ወግ ደርሶኝ የሀይላንድ ውኃ እየጠጣሁ ስብሰባ ስሳተፍ ይህ የመጀመሪዬ ነው። ከነ እማማ ደብሬ ቤት በታች ካለችው ቤተመጽሐፍት ውስጥ የሚገኝ አንድ ስሙን የማላስታውሰው መዝገበ ቃላት “ስብሰባ የሚለው ቃል በቁሙ ሲፈታ ውኃ ውኃ የሚሉ ሰዎች ተመራርጠው የሚሰባሰቡበት፤ በየደቂቃው አፋቸውን በሀይላንድ ውኃ እየተጉመጣመጡ ውኃ የማያነሳ ሀሳባቸውን የሚሰነዝሩበት ፤ በመጨረሻም ከውኃ የቀጠነ ውሳኔ አሳልፈው የሚለያዩበት የሰዎች ጥርቅም ነው ”ይላል።)
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ በተሰጠችኝ ውኃ ንዴቴን አብርጄ አገር ሰላም ብዬ በተቀመጥሁበት ከመርሀግብር መሪዎቹ አንዷ ወደመድረክ ሰበር ሰካ እያለች ወጣችና ቀብረር ብላ “good morning every body welcome to …”አለች በፈረንጅኛ ነው እኮ። አቅለሸለሸኝ ጨጓራዬ ተነሳብኝ፤ በቃ ተቃጠልሁ። ሊነስረኝም አማረው። አሁንም ቀጠለች “….. let’s have some ground rules… first thing is punctuality. Punctuality or timely arrival is a must .” ብላን እርፍ።መቼስ ሰማንያ ደቂቃ አርፍዶ የመጣ ሰው ሰዓት አክባሪ ለመምሰል ሲገዳደር ያልወረደ መብረቅ እራሱም ዘገምተኛ መሆን አለበት።
እንዴው ፈጣሪ አያድርግብኝና የሰይጣን ጆሮም አይሳማ እንጂ ሰሞኑን የጨጓራ በሽታዬ ድጋሜ ከተነሳ ምክንያቱ ከወ.መ.ሽ ሰልፍ እና ቀጠሮ ከማያከብሩ ሰዎች የዘለለ አይሆንም። አይ ወመሽ ወመሽ እኮ ሰልፍ ይወዳል። ካፌ ሰልፍ፣ ሻይ ቤት ሰልፍ፣ ቡና ቤት ሰልፍ፣ ሽንት ቤት ሰልፍ ፣ ሰልፍ ፣ ሰልፍ፣ ሰልፍ ነው ።