Tuesday, June 06, 2017

የማስቲካ እድሜ ስንት ነው?

ባለፈው ቅዳሜ ዕለት ወደ መርካቶ ((የጅማዋን መርካቶ ማለቴ ነው)) እየሄድኩኝ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ሁለት የግቢያችን ሴት ተማሪዎች እኔ የተሳፈርኩበት ታክሲ ውስጥ ከኋላዬ ተቀምጠው ነበር ። ልጆቹን በደንብ አላውቃቸውም ከግቢው በር ወጥተው እኔ ካለሁባት ታክሲ እስከሚገቡ ድረስ እንደከለምኳቸው ከሆነ  ግን አንዲቱ ጠይምና ወፈርፈር ያለች ቁጥር  መልኳ የኔ ቢጤ አፍንጫ ጎራዳ ስትሆን ትክሻዋ ላይ የተዘናፈለው የተፈተለ ሐር የመሰለ ፀጉሯ ቀልብን የመሳብ መግነጢሳዊ ኃይል አጎናፅፏታል። አንደኛዋ ደግሞ ቀላ ያለችና የደም ገንቦ ናት ለማለት ባታስደፍርም የደስደስ ያላት ልጅ ነች።((ከጉልበቱ ላይ የተቀደደ ሱሪ ከመልበሷ በቀር))። 

ልጆቹ ከብዙ ተሳፋሪዎች  ጋር ከቆጪ ወደ መርካቶ የሚሄዱ ሳይሆን በሌላ ዓለም ውስጥ የራሳቸውን ክፍለ ሀገር ፈጥረው የራሳቸውን ህይወት የሚኖሩ ይመስላሉ። የእኛን ታክሲዋ ውስጥ መኖር አለመኖር ከምንም ቆጥረው የመጣላቸውን ሁሉ ያወራሉ። ወዲያው ገብተው ከኋላዬ እንደተቀመጡ “አንደኛዋ  ማስቲካ ከየት አመጣሽ?” አለች ጮህ ብላ። “የቅድሙ ነዋ” አለች ሌላኛዋ በአፏ የያዘችውን ማስቲካ ጧ! ጧ! እያደረገች። “የጥዋቱን እስካሁን እያኘክሽ ባልሆነ” ጥያቄዋን ቀጠለች።“አወና” በማለት መለሰችላት ቀብረር ሞልቀቅ ባለ አነጋግር። “ኧረ ይቅር ይበልሽ እኔ አንድ ማስቲካ ከሁለት ሰዓት በላይ ማኘክ በጣም ነው ሚያስጠላኝ እሽ! አንቺ ደግሞ እየለጠፍሽ ነው እንዴ  ድጋሜ ምታኝኪው?”((እየለጠፉ ማኘክ የሚሉትን ነገር አላረፍሁትም )) ።


“ኧረ ባክሽ እኔ እኮ አንድ ማስቲካ ቢያንስ ለስድስት ሰዓታት ያቆየኛል” ስትል ሽምቅቅ ነው ያልኩት። በልቤ ውስጥ“ግቢያችን የማላመጥ ስፔሻሊቲ ማስተማር ጀምሮ ይሆን እንዴ? ”አልሁና  ዞር ብዬ “ ተይ እንጅ እኔ ተወልጀ ባደግሁበት ሀገር አንድ የስንዴ ክምር  ለመውቃት ስድስት ሰዓት እንደሚፈጅ ነበር የማውቀው” ልላት ፈለጌ ደግሞ በጥፊ ብትልሰኝስ ብየ ዝም አልኩ። የ"Anatomy"  አስተማሪያችን ማስቲካ ወይም ጫት ለረዥም ጊዜ ማኘክ የማላመጫ ጡንቻ ከሚገባው በላይ መወፈር (masseter muscle hypertrophy ) ያመጣል ሲሉ ሰምቻለሁ። የጫጓራ አሲድ ከመጠን በላይ እንዲመነጭ ያደርጋል የሚልም ያነበብኩ መሰለኝ። ኧረ ለመሆኑ ግን የአንድ ማስቲካ እድሜው ስንት ነው? ማስቲካን  ለረዥም ጊዜ ያለቋርጥ ማላመጥስ ጥቅሙ ምን ይሆን?

እንደ ሥራፈትነት የማይታይብኝ ከሆነ ስለ ማስቲካ ሲነሳ ከማስታውሳቸው ገጠመኞቼ አንድ ሁለት ልበል። አሁን በቀደም ዕለት ከአንድ ጓደኛዬ ጋራ የሆነ ሱቅ ሄድንና  ከኪሱ ያገኛትን የአንድ ብር ሳንቲም አውጥቶ  እያሳየ  ማስቲካ  እንድትሰጠው ባለሱቋን ጠየቀ። ባለሱቋም ጦር ይሁንል ወይስ.......? ስትለው በጣም ከመደንገጡ የተነሳ ከስሩ እንደቆረጡት ዛፍ ሲንገዳገድ ልጅቱ ደንግጣ ዞር በማለቷ እንደ መትረዬስ የተቀሰሩ ጡቶቿ እና የበሰለ ቲማቲም የመሳሰሉ ከናፍሮቿ ደጋግፈው ከውድቀት አዳኑት። ለደቂቃዎችም አጫዎቱት። እኔ ምለው እንዲያው አንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢዎች ይህንን ጦርነት ወዳድ ህዝብ በጦር ስም አታልለው በአቋራጭ ለመክበር የጠነሰሱት ሴራ ካልሆን በቀር አሁን ጦርና ማስቲካን ምን አገናኛቸው???

ጓደኛዬ ማስቲካውን ከጦርነት ወደ ሙዝነት አስቀየረውና ከሁለት ከፍሎ ረዘም ያለውን ለራሱ ያዘ አነስኛዋን ለእኔ ሰጠኝ። እንደ መግደርደር እኔ እኮ ማስቲካ ማኘክ አልወድም ስለው “ያዝ ባክህ ምኑ አይታወቅም አንዲቱ ሳመኝ ያለችህ እንደሆነ ጫማ ጫማ በሚል አፍህ ከምትስማት ተዘጋጅተህ  መጠበቁ ይሻላልሃል ብየ ነው ብሎኝ እርፍ።” ((ወይኔ ቀጭኑ ይሄ ጭብጦ ፊት እንዴት አባቱ ቢንቀኝ ነው ግን እንደዚህ በሴት ፊት የሚያዋርደኝ?))

ሁለተኛውን የማስቲካ ትዝታዬን ተከትዬ ሶስት አራት አመታትን ወደ ኋላ ሳፈገፍግ እራሴን "biochemistry laboratory "ውስጥ አገኘዋለሁ። “የዚች ድሃ ሀገር እጣ ፋንታ  ነገ  እጄ ላይ የሚጣልብኝ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ነኝ”በሚል ጠንካራ መንፈስና ወኔ አዲስ ጋውን ለብሼ ወደ ሀምሳ የሚጠጉ ጓደኞቼ ጋር አንዱን ኬሚካል ከሌላው እያቀላቀልኩ።አንዲት የክፍል ጓደኛየ ከግራ ጎኔ ረጅም ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ((ተንጠልጥላ ማለት ይሻላል)) ይህን መከረኛ ማስቲካ ጠሽ! ጧ! ጠንቦሽ! እያደረገች ለአምስት የትምህርት አይነቶች ማስታወሻነት እንዲበቃ ተደርጎ በተሰራው ደብተሯ ላይ የፃፈችው አጤሬራ  ትቸክላለች።

የምታኝከው ማስቲካና ከደቂቃዎች በፊት የበላችው ፓስታ ተደማምረው  የትንፋሿን ጠረን ለሳምንታት ያለማቋረጥ የምግብ ትራፊ ሲደፋበት ከሰነበት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ገንዳ እንጂ ከሰው አፍ የሚወጣ እንዳይመስል አድርገውታል።ድንገት ሀፍረት ይዟት ትተወው እንደሆነ በሚል እሳቤ “ይቅርታ ሲስቱ ድምፅሽን ትቂት ትቀንሽልን?” ልላት አስቤ ነበር።ነገር ግን “እዚህ ላብ ውስጥ "handout" ይዘህ ገብተህ ስታነብ ወይም የጎንዮሽ ወሬ ስታወራ ባገኝህ አንተን አያርገኝ "sulphuric acid" ነው ምደፋብህ!”የሚለውን የጋሽ እንትናን ዛቻ ፈርቼ ዝም አልኩ።

ልጅቱ በቶሎው የምትተው አይነት አልነበረችም አሁንም ጠሽ! ጧ! ጠንቦሽ! እያረገች መውቃቷን ቀጥላለች።ምርር ብሎኝ ቀና ብዬ ሳያት የሆነ የተነፋ ኮንዶም የመሰለ ነገር በሊፕስቲክ በደመቁት ከንፈሮቿ ስትወጥር ደረስኩባት። ከዚያች ቀን በፊት እንደዚያ አይነት አስነዋሪ  ነገር አይቼ አላውቅም ነበርና ማቅለሽለሽ ሲጀምረኝ ክፍሉን ለቅቄ  ወጣሁ ። ላብ በላብ ሆኘ ባዶ ሜዳ ላይ መውደቄን ያወቅሁት ከግማሽ ሰዓት በኋላ ነበር ። በክፍላችን ካሉት ሴት ተማሪዎች የተሻለ ደምግባት ያላት ልጅ ብትሆንም ቅሉ እሷን ባየሁ ቁጥር ያ የተወጠረ ነገር እየታየኝ  ያ መጥፎ ሽታም እየሸተተኝ  እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደ አባጨጓሬ እጠላትና እጠየፋት ነበር። እርሷ ግን ይህንን የምታውቅ አይመስለኝም ማወቅም አይጠበቅባትም ይህንን ማወቋ ይጎዳት እንደሆን እንጅ  አይጠቅማትምና ።


ጌች ቀጭኑ ከገዳም ሰፈር 
ግንቦት 27/2009 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment