ይህ ዘመን እመቤታችን ከኢየሩሳሌም ውጪ የኖረችበት ዘመን ነው ፤ጌታ በተወለደ በሁለት ዓመቱ ሰብአ ሰገል በመጡበት ወራት ከሄሮድስ ቁጣ የተነሳ ድንግል ከነ ልጇ በከተማ መቀመጥ አልቻለችም።ሰይጣን የሰው ልጆችን የመዳን ስራ ሲጀምር ሲመለከት ዝም አላለም፤ገና ይወርዳል፣ይወለዳል፣ሲባል ትንቢቱን በመስማቱ እነ ኢሳይያስን በመጋዝ አስተርትሮ ፣በኩላብ አሰቅሎ አስገድሎ ነበር። ሲወለድም የተወለደውን ሕጻን ማሳደድ ጀመረ። በተለይም ሊወለድ ሃያ አምስት ቀን ሲቀረው መላእክት የሚወለድበትን ስፍራ ቤተልሔምን ተገተው ይጠብቁ ነበርና አጋንንት በጣኦታት አድረው መመለክ ስለተሳናቸው ጣኦታቱም ወድቀው ወድቀው በማለቃቸው ይህንን ምልክት አድርጎ ዲያብሎስ አዳኝነቱን ጀመረ።
የአባቶቻችን አዳኝ እርሱ በእመ አምላክም ላይ ከሰው እስከ አጋንንት የክፋት ሰራዊቶችን አስከትሎ ለሰልፍ ተነሳ ። አስቀድሞ በመጽሐፍ ለዚች ቀን የተነገረው የመጀመሪያው ትንቢታዊ ቃል በዚህ ጊዜ ተፈጸመ። "በአንቺና በሴቲቱ በካከል በዘርሽና በዘሯም ላይ ጠላትነትን አደርጋለሁ" ይህ ቃል በገነት ውስጥ ከተነገሩ የወደፊት የሰው ህይወት ጠቋሚ ቃላት አንዱ ሲሆን እመቤታችንና "የቀደመው እባብ" ተብሎ በሚጠራው ጥንተ ጠላታችን በሰራዊተ አጋንንት እና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መካከል የሚደርገውን ጦርነት የሚያመላክት ቃል ነው ።