ባህር ወደታች ምን ያህል ጥልቅ ነው? ዓለምስ ወደጎን ምን ያህል ይሰፋል? ፀሐይ ምን ያህል ትርቃለች? ከዋክብት ምንኛ ይበዛሉ? የሰው ልጅ ልቦና ምን ያህል ርቀት ይመሰጣል? አእምሮው እስከየቱ ጥግ እስከምን አጥናፍ ድረስ ያስባል? ሁሉም ወሰን አለው። ሁሉም ዳር ድንበር ጥግ አለው።ምድር ምንም ፍጹም ነገርን እንደማታስተናግድ ትባላለች። ፍጽምና የለባትም ይባላል። ሁሉም ጎዶሎ እንደሆነ ይነገራል። ሁሉም ሙሉ ለመሆን አንዳች ሌላ ግብዓት ይሻል። ቀን ያለፀሐይ፤ ምሽት ያለ ጨረቃና ከዋክብት፤ ዝናብ ያለደመና፤ ደስታ ያለመከራ፤ ድል ያለውጊያ አይገኙም። ዓለም ራሷ ምኗም ሙሉ አይደለም። አንዱ ከአንዱ ጋር ይደጋገፋል።ትዕግስት ጠረፍ አለው፤ ጽናት ገደብ አለው፤ ሸክም ልክ አለው። የሰው ልጅ «ከዚህ በላይ አልችልም፤ ከዚህ በላይ አልታገስም፤ ከዚህ በላይ ይከብደኛል» የሚለው ጠርዝ አለው። ይደክማል። ይሰለቻል። ቢታገስ እንኳን ያማርራል፤ ቢጸናም ተስፋው ይዝላል፤ ቢሸከምም ደርሶ አውርዶ ሊጥል ይናፍቃል።ሰው ስልቹ ነው። ሰው ወረተኛ ነው። ዛሬ የያዘው ወርቅ ነገ መዳብ ይመስለዋል። ዛሬ ያመሰገነውን ነገ ሊኮንነው ይችላል፤ አሁን ለሳቀለት አፍታም ሳይቆይ ይነክሰዋል። ሰው ወረተኛ ብቻ አይደለም። ደግሞም ራሱን ወዳድ ነው። ለእርሱ እንደተመቸው ብቻ፤ ለእርሱ እስከሆነለት ብቻ ነው ምንም ነገር ቢሆን የሚፈልገው።