Tuesday, March 17, 2020

ፀባይ

“ቢያንስ በፀባይ ማስተናግድ ትችል ነበር” ይለኛል የማንም ወመኔ የቤቱን ጉድ ሁሉ አግተልትሎ እየመጣ
.
ለመሆኑ በአሁኑ ሰዓት ያለን ኢትዮጵያዊ  ሀኪሞች ከሌላው ሰው የተለየ ትዕግስትና ትህትና እንዲኖረን የሚጠበቀው ለምንድን ነው? አስራ ስምንት ዓመት ሙሉ ተምረን ስለምትከፈለን ለቤት ኪራይ የማትበቃ ደመወዝ (6179) ነው ? እንደ ጅብ ሌሊቱን ሙሉ ስንጓዝ አድረን ስለምናገኛት ለዚያውም በስንት ልመና ስለምትመጣው የተረኝነት አበል ነው? የላቦራቶሪ ግባቶችና የህክምና መሳሪያዎች በሌሉበት አስታማሚዎቹ ሲያለቅሱ አብረን ከማልቀስ ውጪ ምንም ማድረግ በማንችልበት ባዶ ህንፃ ውስጥ ተቀምጠን የጤና መድህኑን ብቻ አንጠልጥሎ የመጣን ከሞት አፋፍ ላይ ያለ ታካሚ እያየን  ስንጨነቅ ስለምንውል ነው? ቆይ ምን አድርጉ ትሉናላችሁ ?
.
ሁሉም በየቤቱና በየመሥሪያቤቱ ጉዱን አስቀምጦ “ሆስፒታል” ሲመጣ እራሱ ላይ ፈልጎ ያጣውን ጨዋነት ሀኪሙ ላይ ካላገኘሁ ሞቼ እገኛለሁ ይላል። ስታሳድገኝ ያላስተማርከኝን ጨዋነት ከየት እንዳመጣው ትፈልጋለህ? ያኔ አስፓልት ላይ አንበርክከህ እንደ ሌባ አርባ ጊዜ አስገርፈኸኝ ዛሬ ለምን ፊትህን አጠቆርክብኝ ብለህ ያዙኝ ልቀቁኝ ስትል ትንሽ አይሸምምህም? ሂድና ይችን ምርመራ አስረትህ ና እምቢ ነው! ይችን መድሃኒት ከውጭ ግዛና ውሰድ “ያንተ መነገጃ አድርገኸኝ” ነው! የላቦራቶሪና የህክምና መሳሪያዎች ይሟሉልን ብለን ጥያቄ ስናነሳና ድምፃችንን ስናሰማ ህዝብና መንግሥት እየተቀባበሉ “ሀኪሞች ጠግበው ሥራ አቆሙ” ነው ። “ልትወልድ የመጣች እናት ትተው ሰልፍ ወጡ” ነው። ባልታደለ ዘመን በግም ወቅት ተፈጥረን በሁለት ወጥመድ የተያዘች ቆቅ ሆነን አርፍናትኮ ጎበዝ !!!
.
©ዶ/ር ጌታነህ ካሴ
ፍ/ሠላም ሆስፒታል

ዘመቻ

አንት የኮስትር አሽከር የቴዲ አልጋ ወራሽ ስማኝ ወንድም ጋሸ
በለስላሳ አንደበት በቅቤ አንጓች ምላስ ቀርቦ እያሞካሸ
ሊያጀልህ ቢሞክር የማንም ወስላታ
አቤት ወዴት ብለህ ትጥቅህን አትፍታ
ሚስትህን ከሽፍታ ታግለህ እንድታስጥል
ሽመል ከዘራህን ከክንድህ አትነጥል
እምቢ በል ጀግናዬ ፎክር እንደ አባትህ
በባንዳ ከሃዲው በሰላቶው ሁሉ አይደፈር ቤትህ
አስከትለኝና ዝመት ወደ ጫካው እንሂድ ወደ ጋራው
በክንድህ ብርታት ነው የነፃነት ጮራ ፀሐይህ ሚያበራው
ልጅህን ተዘርፈህ ምንድን ነው ዝምታ
ክንዳለሜ እያለች እህትህ ታግታ
ውርደትን ታቅፎ ምንድን ነው ምኝታ
እስከ መቼ ትዕግስት እስከ መቼ ዛቻ
እስከ መቼ ድረስ የቃላት ጦርነት የስድብ ዘመቻ
እንዲህ የጭንቁ ዕለት
እንዲህ በክፉው ቀን ልብህ ካልጨከነ
ሦስት ዙር ዝናርህ ምኑን ዝናር ሆነ
ምኑን ነፍጠኛ ሆንክ ምኑን ትምክህተኛ
በርህን ሲቆረቆር አጥርህ ሲነቀነቅ ልብህ እየተኛ
.
.
.
ወይ ነዶ