ወደታች ስንት
ነው የባህር ጥልቀቱ?
ዓለምስ ወደጎን
ስንት ነው ስፋቱ?
መሬትና ፀሐይ ስንት ይራራቃሉ?
የሰማይ ከዋከብት እንዴት ይደምቃሉ?
የሲዖል ጨለማ ምን ያህል ይጠልቃል?
የሰው ልጅ
ልቦና ምን
ያህል ይመጥቃል?
አእምሮ ቢጠበብ
እስከ የት ጥግ ያውቃል?
ሁሉም ወሰን
አለው አብጅቷል ዳር ድንበር፣
ፍፁም አይደለችም
ደምቃ አትቀርም ጀንበር።
ሁሉም ጎደሎ
ነው ይሻል ሌላ ግባት ፣
ትዕግስት ጠረፍ አለው ገደብ አለው ጽናት ፣
ምኗም ሙሉ አይደለም ዓለምም ባዶ ናት፤
ቀንም ያለ
ፀሐይ ሌት ያለ ጨረቃ፣
አቅም የላቸውም
ድኩም ናቸው በቃ።
አድሮ ይቀየራል ሰው ወረተኛ ነው፣
ውዱን ያሞካሻል ነገ ሊኮንነው።
ፍጥረት ግፈኛ ነው እራሱን ይወዳል፣
ህሊናውን ክዶ ጥቅሙን ያሳድዳል።
እስከማላውቀው
ጥግ የሚወድሽ ሆዴ፣
ታዲያ እኔ ምንድን ነኝ ሰው አይደለሁ እንዴ?
በማዕረግ ብመረቅ ብሆን ተሸላሚ፣
ሪከርድ በመስበር ሰውን አስደማሚ፣
ፍጥረት የሚያደንቀኝ ብሆን የሰው ጀግና፣
ትንሹም ትልቁም የሚያውቀኝ በዝና ፤
ተሸናፊም ብሆን ምስኪን የሰው ተራ ፣
ከአስጨብጫቢዎች ጋር ስሜ ማይጠራ፣
ተገፍቸም ብወድቅ ይች ዓለም ብትክደኝ፣
ከምወድሽ በላይ ልብሽ የሚወደኝ፤
ምኞት ምርቃትሽ የሆነኝ መከታ፣
ቁጣና እርግማንሽ በ’ኔ ማይበረታ፣
እስኪ መልሽልኝ ልጠይቅሽ ለአፍታ፤
ሳይበሉ የሚያጠግብ ስምሽን ሲጠሩ፣
ወሰን አልባው ፍቅርሽ ምንድነው ምስጢሩ?
ሲያስቡሽ ፈገግታን ደስታን
የምትሰጭ፣
በቀዝቃዛ ዓለም ውስጥ ሙቀት የምትረጭ፤
ውለታ ማትቆጥሪ ወረት የማታውቂ፣
ስለ አብራክሽ ክፋይ የምትጨነቂ፤
ድህነት ቢይዘው እጅሽን ጨምድዶ፣
ገላሽ በጋሬጣ እንደ ፍየል ታርዶ፣
የማይታጠፍ ክንድ ተንቆም ተዋርዶ፤
የማይደክም ወገብ የማይዝል ትክሻ፣
አቅፎ የሚደግፍ እስመ መጨረሻ ፤
የደፈረሱ ዓይኖች በጭስ የጠገጉ፣
ሸካራ መዳፎች በእሾህ የተወጉ፤
ጎስቋላ ግርባቶች ጫማ የማያውቁ፣
ሰንጣቃ ከናፍርት በብርድ የደረቁ፣
እስኪ ቢፈቅዱልኝ ዛሬስ ይጠየቁ።
ጥግ የሌለው ጽናት ተስፋው ያልተነካ፣
ልጅሽ የማይመስልሽ በልቶ የሚረካ ፤
ለእርሱ የተኖረ የእድሜሽ እኩሌታ፣
ሁሌም በመጨነቅ ዘወትር ጧት ማታ፤
ሊገልፅ የማይችለው የብዕሬ ጠብታ፣
ትርጓሜው ምንድን ነው የፍቅርሽ አንድምታ?
አፍሽን ክፈችው እስኪ እንነጋገር፣
ወረት የማይገዛሽ ባትሆኝ ገራገር፣
ለውለታሽ ምላሽ ምን ይከፈል ነበር?
©ጌች ቀጭኑ: ለእናቴ ወ/ሮ ትሁኔ ዋሴ
ነሐሴ 27/2009 ዓ.ም