Saturday, January 30, 2016

አስተርእዮ ለማርያም

በዓሉ አስተርእዮ መባሉ ግን ሁለት ነገርን ያሳያል አንድ ወራቱ ማለት ጥር ጌታችን በጥምቀቱ ምስጢረ ሥላልሴን ከዚያም ጋር አምላክነቱን ለዓለም የገለፀበት በመሆኑ ሲሆን ሁለተኛ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በወለደችበት ስብሐተ መላእክትን በሰማችበትና ባየችበት የልደት ወራት  አካባቢ ከዚህ ዓለም በሞት ተለታ ወደ ሰማይ ስትወጣ በስማይም በምድርም ለሰውም ለመላእክትም  ከልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ አብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣት ጸጋና ክብር መገለጡን ያሳያል "አስተርእዮ" ማለት መታየት መገለጥ ማለት ነውና።የኢትዮዽያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ ቅዱስ ያረድ አምላክ ከድንግል በሥጋ መወለዱን በዚህም በአካለ መጠን ለዓለም መገለጡን አተርእዮ ብሎ ሲናገር ሌላው ደግሞ{ደራሲ ሊቅ }የትንቢት አበባ እግዚአብሔር የእኛ ሥጋ የሆነውን ያንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደተገለጠ ለእኛም እንደታወቀ ድንግል ሆይ የመገኛችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ በፍጹም ደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግንሻለን ብሏል።እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥር 21 እሁድ ቀን በ49 ዓ.ም በ64 ዓመቷ አርፋ ከዚህ ዓለም ወደ ዘለዓለማዊ ህይወት በምትሸጋገርበት ዕለት{በዕረፍቷ ቀን} ቅዱሳን ሐዋርያት አስከሬኗን ወደ ጌተሴማኒ መቃብር በሚወስዱበት ጊዜ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና ከዚህ ቀደም ልጇን ኢየሱስን "ሞተ፣ ተነሳ፣ አረገ ደግሞ በክፉወችና በበጎወች ለመፍረድ ይመጣል" እያሉ ሲያውኩን ነበር። አሁን ደግሞ ይህችን እናቱን ዝም ብንል "ሞተች ተነሳች" እያሉ ሊያውኩን አይደል አሁንም "ኑ በእሳት እናቃጥላት" ብለው ከእነርሱ መካከል አንዱ ታውፋኒያ ወይም ሶፍንያስስ የሚባለውን ልከው አስከሬኗን ለማቃጠል የተጠቀሰው ሰው ተረማምዶ በድፍረት የአልጋውን ሸንኮር ሲጨብጥ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሁለት ትክሻው በሰይፍ ቀጣው። ሁለቱ እጆቹም ከአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ።ይህም ቅጣቱ ስላስደነገጠው በይበልጥም ምክር ስለሆነው ወዲያውኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ አምላክ እርሷም ወላዲተ አምላክ መሆኗን አምኖ በልጇ ቸርነት በእርሷ አማልጅነት ተማምኖ ምህረትና ይቅርታን ስለለመነ በቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት በእመቤታችን አማላጅነት እጁጆቹ እንደነበሩ ተመልሰውልታል።ሥጋዋንም ቅዱሳን ሐዋርያት ለጊዜው ጌቴሴማኒ በተባለው ቦታ አሳርፈውታል በሶስተኛው ቀን ግን መላእክት ከዚያ አፍልሰው  በገነት በዕፀ ህይወት ስር አኑረውታል።ከመቃብር እስከተነሳችበት ዕለት ድረስ ለሁለት መቶ  አምስት ቀኖች በዚያው ቆይቷል።ክርስቶስ ለሚመጣበት ለ2500 ዓ.ም ምሳሌ ነው። 200 የ 2ሽህ 5ቱ የ500 በዚህ ጊዜ የሰው ሁሉ ትንሳኤ ይሆናል።በዕለተ እረፍቷ ብዙ ፍጹም በረከት ተሰጥቷል።የፈውስ ጸጋ ከደረሳቸው አንዱ ታውፋንያ ነው።በዚህ ዕለት የተደረገውን ሁሉ የታሪክ መጻህፍት ዘርዝረው ያስረዳሉ።በዚህ የተጠቀሰው ግን በአጭሩ ነው።ስለዚህ በእረፍቷ ምክንያት ጥር 21 ቀን የተጀመረው በዓል መታሰቢያ በየወሩበ 21 ቀን እንዲታሰብ የኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ስለሆነ ወሩ በገባ በ21ቀን የእረፍቷ በ29 ቀንም አምላክን የመውለዷ መታሰቢያ ይከበራል።ይህም በቀድሞ መባቻ በዓል ፈንታ የገባ ነው። ያ ጥላ ምሳሌ ስለነበር አምናዊ ተተክቶበታል።

                                                                        ምንጭ፦መጽሐፈ ታሪክ ወግስ

Wednesday, January 27, 2016

ቀና በል ቀን አለ

ሽንፈትህ ቢነገር ገዝፎ እንደ ተራራ፣
ስህተትህ ቢተረክ መውደቅህ ቢወራ።
ተዋርዶም ተንቆም ሰው መሆን ስላለ፣
አንገትህን አትድፋ ቀና በል ቀን አለ።

             ይህ ግጥም ከ"hand out" ጀርባ ላይ የተገኘ ነው ።

Tuesday, January 12, 2016

ጣፋጭ ፍሬን ላፍራ

የልቤን ቋጠሮ ቂም በቀል አንስተህ፣
ክፋት ምቀኝነት ቁጡነቴን ፍቀህ፣
መራሩን አንደበት በጣፋጭ ለውጠህ፣
ቀና ሰው እንድሆን ይጎብኘኝ መንፈስህ።
ቁጥቋጦ ቋጥኙ ይመንጠር ይወገድ፣
ሸክፈው ምላሴ በቃልህ ይሞረድ፣
ጉልበቴ ይንበርከክ ሰውነቴም ይራድ፣
መንፈስህ ይኑረው በልቤውስጥ መንገድ።
ቀዳዳው ተደፍኖ  ጎድጓዳው ይሞላ፣
ትዕቢትን ይናቀው ጥልቻንም ይጥላ
ትሕትናን በመልበስ ጥል ከእሱ ይከላ፣
መቅደስህ እንዲሆን መላው የእኔ ገላ።
ሕሌናዬ ሁሉ በጎ ነገር ያውጣ፣
በፊትህ የሚኖር ከህግህ ያልወጣ።
መልካም መሬት ይሁን የልቦናየ እርሻ፣
ጥፋጭ ፍሬን ላፍራ እስከመጨረሻ።


                      ምንጭ ፦ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነሐሴ 2004ዓ.ም

Friday, January 08, 2016

ተወልደ ኢየሱስ በቤተልሔም ዘይሁዳ

 

      በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተደረገልን ሥርየትና ዕርቅ ግልጥ ሆኖ የተጀመረው በነገረ  ልደት ነው።የጌታችን ልደት በነገረ ድኅነት ትልቅ ስፍራ የያዘና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ፍጹም ልዩ መሆኑን ያሳየ ነው።መስተፃርራን የነበሩ ሰማይና ምድር፣ሰውና መላእክት በአንድነት ለምስጋና ታድመዋል።የእረኞች አንደበት  ከመላእክት ጋር ለሰማያዊ ምስጋና ብቁ የሆነበት፣ግዕዛን የሌላቸው እንስሳት ሰራኢ መጋቢያችን፣በዘባነ ኪሩቤል በሰማያት የምትገለጥ አንተ ነህ ሲሉ እስትንፋሳቸውን የገበሩለት፣የምድር ነገስታት በስልጣንህ ሽረት በመንግስትህ ህልፈት የሌለብህ የነገስታት ንጉስ አንተ ነህ ሲሉ ወርቅን ለመንግስቱ፣ዕጣንን ለክህነቱ፣ከርቤን ለሕማሙ ዕጅ መንሻ ያበረከቱለት፣ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ከጻድቁ ዮሴፍ ጋር ያን ልዩ ክብር ያዩበት፤ይህ ልደት በእውነት ልዩ ነው።ቅዱስ ኤፍሬምሶሪያዊ በረቡዕ ውዳሴ ማርያም በጌታ ልደት የተደረገልን ድንቅ የማዳን ስራ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ ነበር ያለው፦"በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤በቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህንን ድንቅ እዩ፣ስለተገለጠልን ምስጢር ምስጋና አቅርቡ ሰው ያማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋህዷልና ቅድምና የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት።" ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ይህች ቤተልሔም መንግስተ ሰማያትን መሰለች" አለ፤የጌታን ልደት በተናገረበት አንቀጽ።በአባታችን በቀዳማዊ አዳም ምክንያት ያጣናትን ልጅነት ሊሰጠን ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ የመንግስተ ሰማያትን የምስጋና ኑሮ በቤትልሔም ገልጧልና።ስለዚህ ነገር ነብየ እግዚአብሔር ሚክያስ  "አንቺ ቤተልሔም ኤፍራታ አንቺ ከይሁዳ አእላፍ መካከል ትሆኝ ዘንድ ታናሽ ነሽ  ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞው ጀምሮ ከዘላለም የሆነ በእሳራኤል ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልና.." በማለት የተነበየውም ስለዚህ ነበር፤ሚክ5፡2 "ወአንቲኒ ቤተልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሃቲ እምነገሥተ ይሁዳ እስመ እምኔኪ ይወጽእ ንጉስ ዘይርዕዮሙ ለህዝብየ እስራኤል" እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም።

Wednesday, January 06, 2016

የዓለም ድኅነት በክርስቶስ ልደት

ቤተክርስቲያናችን የምትቀበላቸው አምስት ዓበይት ምስጢራተ ቤተክርስቲያን መኖራቸው የታወቀ ነው።እነርሱም "አምስቱ አዕማደ ምስጢር" በሚል ስያሜ ይጠራሉ። ከእነዚህም ታላላቅ ምስጢራት አንዱ ምስጢረ ስጋዌ ነው። "ምስጢር" የሚለው ቃል በቤተክርስቲያናችን  አነጋገር በፍልስፍናዊ ርቀትና በምርምር ሳይሆን፤በእግረ ሕሊና ብቻ ሊደርሰበት የሚቻል ነገር እንደሆነ ይታመናል።ስለዚህ ምስጢረ ሳጋዌ ማለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ቃል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ መላውን የሰው ዘር ለማዳን ሲል ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው የሆነበት ምስጢር ነው። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የሚደነቅ እንጂ የማይመረመር ታላቅ ምስጢር ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሰው ሆኖ መላውን የሰው ዘር ከድቀተ አዳም ጀምሮ [5,500]አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሙሉ በሃጢአት አዘቅት ተጥሎ የቅጣት ማዕበል እየወረደበት፤በእግረ ሰይጣን እየተረገጠ የቁም ሙት ሆኖ ሲኖር እንደዚሁ ቃላት ሊገልጹት ከማይችሉት ኀዘንና ስቃይ፤እንዲሁም ተስፋ መቁረጥ ያድነው ዘንድ ስለተወለደ፤የአባቱን ፈቃድ በመፈጸም የሰውን ደዌና ሕማም ተሸክሞ፤ሥጋን ለብሶ ሰው በሆነም ጊዜ መላው የሰው ዘር በመከራ ይኖር ዘንድ ተነግሮ የነበረው አዋጅ ተሻረ። "አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ" የሚለውም መዝገብ ተቀደደ፤በኀጢአት ፈንጋይነት ታፍኖ ተሽጦ የነበረው አዳምም ወደ ጥንተ ክብሩ ተመልሷል።


በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ፍቅሩ፣ጸጋውና ይቅርታው ተገልጿል። ከፈጣሪው ቅጽረ ረድኤት ውጭ ሆኖ የነበረው አዳም ወደ ጥንተ ቦታውና ማዕረጉ ክብሩና ሞገሱም ተመልሷል። በሰማይና በምድር መካከል የዕርቅና የይቅርታ ሰንደቅ አላማ ተተክሏል። ከፈጣሪው ጋር እንዲሁም ከራሱና ከአካባቢው ጋር ተጣልቶ ይኖር የነበረው ፍጡርም ታርቋል። ይህም ዕርቅ ምን ማለት እንደሆነ ለመግለጽ ያህል ኦሪት ዘፍጥረት3፡23 አዳም የፈጣሪውን መንግሥት ለመገልበጥ ባደረገው አመጽና፡መቀናቀን የሞት ሞት ተፈርዶበት ከገነት ሲወጣ ዱሮ በትእዛዙ ሲተዳደሩ ይኖሩ የነበሩት አራዊትና እንስሳት ሁሉ አፋቸውን ከፍተው አስፈራሩት ቀንዳቸውንም አሹለው ሊወጉት ቃጡ። በጥፍራቸው ኃይል የሚጠቀሙት እንዲሁ ጥፍራቸውን አዘርዝረው ሊቧጥጡት ቀረቡ ይላል። ይህም አዳም ባደረገው ጥፋት ተጣልቶ የነበረው ከእግዚአብሐር ጋር ብቻ ሳይሆን ከአካባቢውም ጋር እንደነበር ያስተምረናል። በተጨማሪም ከዚህ በላይ በወንጀለኛ ላይ የሚፈርደው ዳኛ ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ፣ወዳጅና ዘመድና ባዕድም ጭምር እንደሆነ እንረዳለን። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከተወለደ በኋላ ግን የሰው ኀዘኑ ወደ ፍሥሐ ተለውጧል።በጠቅላላው ልደተ ክርስቶስ  ነገደ አዳምን በሙሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ አውጥቶ ከአካባቢውና ከመላው ሥነ ፍጥረት ጋር ከነበረው ቂምና በቀል እንዲሁም ጠላትነት አስታርቆ የራሱንም የሕሊና ባርነት ድል እንዲነሳ አድርጎ የእግዚአብሔር ልጅ ለመሆን አብቅቶታል።