Wednesday, July 12, 2017

ምጥን

እስካሁን ከማውቃቸው ደጋግ  ሴቶች አንዷ ነች።የይርጋለም ተወላጇ እና 2ኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪዋ ምጥን ሃይረዲን ። ዛሬ ሚያዚያ 14 ቀን 2009 ዓ.ም ከምሽቱ 11:40 ላይ የአባላት ጉዳይ ስብሰባ ለመሳተፍ ወደታች ቤት ስሄድ እሷም እዬሄደች ኑሮ የግቢው መውጫ በር ላይ ተገናኘን።ሰላምታ ተለዋውጠን ትንሽ አብረን እንደተጓዝን የምታደርሰው እቃ እንዳላት ነግራኝ የሆነ ሱቅ ደርሳ ተመለሰች።

ስትመለስ እንደ አካሄዷ ብቻዋን አልነበረችም አንዲት በግምት 8 ወይም 9 ዓመት የሚሆናት ህጻን አስከትላ ነው የመጣችው።ህፃኗ በስስት ዓይን ሽቅብ ሽቅብ እያየች ትከተላታለች። በደብተሯ ጀርባ ላይ አድርጋ በነጭ ፔስታል የተቋጠረ የገብስ ቆሎ ይዛለች። ለመስጠት አልመች ስላላት መሰለኝ ያዝልኝማ አለችና ደብተሯን እና ቆሎ የተቋጠረበትን ፔስታል አስታቀፈችኝ ። ስይዝላት ቋጠሮውን ፈትታ በአንድ እጇ እያፈሰች አብራት ለመጣችው ልጅ ሁለት ጊዜ ሰጠቻት። ልጅቱ ሁለት እጆቿ ቆሎውን መያዝ አቅቷቸው እየተቸገረች ካጠገባችን እንደቆመች ሁለት ሶስት ጊዜ ቃም ቃም አደረገችና በሀሴት ተሞልታ እየሳቀች ከፊታችን ተሰወረች።እኛ እዚያው ቆመን እያለን አንድ በእድሜ ጠና ያሉ የኔ ቢጤ የተቀዳደ ጃኬት ለብሰው ከመኪናው መስመር ባሻገር ተቀምጠዋል።“ለእኒያ ሰውዬ ልስጣቸው ወይስ ጥርሳቸው ያስቸግራቸው  ይሆን?” አለች በጣም እንዳሳዘኗት ከፊቷ ይታወቃል። “አይ ይበሉ ይሆናል ጠይቂያቸው እስኪ” አልኳት። ቆሎውን ከነፔስታሉ ተቀብላኝ መስመሩን በሩጫ አቋርጣ ሄደች “ኧረ መኪና እንዳይገጭሽ” ስላት አልሰማችኝም። ቆሎውን ከነፔስታሉ ለሽማግሌው ሰጥታ አሁንም እየሮጠች መጣች።መሮጥና መሳቅ ትወዳለች ስትሄድ መሮጥ ስትመጣ መሮጥ ስታገኝም ስታጣም ስትደሰትም ሲከፋትም መሳቅ ነው አመሏ።

ሁሉንም ሰጠሻቸው?”አልኋት “አዋ” አለች በደስታ እየተፍለቀለቀች።“ትገርሚያለሽ ለእኔ ታስተርፊልኛለሽ ስል እንዴት ሁሉንም ትሰጫቸዋለሽ?” ። “እንደምትበላ መች ነገርከኝ?” አለች። “እነርሱ ነግረውሽ ነው?” አይ እነርሱማ እንደሚያስፈልጋቸው ስለማውቅ አስቤበት ነው ከቤቴ ይዠ የመጣሁት” አለች ። ከሱቅ የገዛችው መስሎኝ ነበር እንጂ አስባበት ከዶርም ይዛላቸው መምጣቷን አላወቅሁም ነበር።“እና አንተ አያስፈልግህም እያልሽኝ ነው” አልኋት  “እና በቃ ሌላ ጊዜ ይሰጥሃላ” አለች አትጨቃጨቅ በሚመስል ዜማ።

 እኔም እየቀለድሁ እንደሆነ ነግሪያት በጣም “ደግ ልብ ነው ያለሽ የእውነት አንቺ ጥሩ ሰው ነሽ ሳላመሰግንሽ  አላልፍም።”አዬህ ይሄ ቆሎ ለእኔ ሁለተኛ ነው ቢያንስ የካፌው ምግብ እኔን ሊያጠግበኝ ይችላል።ለእነሱ ግን ይህ ትልቅ ነገር ነው ።ሌላ ተስፋ የሚያደርጉት የላቸውም። ለዚያ ነው ከቤተሰብ የተላከልኝን ለእኔ ይቅርብኝ ብዬ  ይዠላቸው የመጣሁት።ደግሞ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ እንደዚህ አደርጋለሁ።” አለች ቀለል አድርጋ ነው የምትናገረው።

በጣም እየተገረምኩ “የእውነት ደግ ልብ ነው ያለሽ እንዳንቺ አይነት ልብ ለሁላችንም ቢያድለን ምንኛ ጥሩ ነበር አልኩ ።”ከልቤ ነበር። “አየህ  እኔ ችግርን ስላየሁት አውቀዋለሁ ለዚያ ነው መሰለኝ...” ብላ ልትናገር የፈለገችውን ሳትጨርስ ዝም አለች።ድምጿ ቀዝቀዝ ብሏል ከኋላየ ነበረችና የፊቷን ገጽታ ማዬት አልቻልኩም። ቆም ብዬ ጠበቅኋትና ጎን ለጎን መጓዝ ስንጀምር “ችግርን ያላዬ ይኖራል ብለሽ ነው?” አልኋት ስሜቷን ለማጤን እየሞከርኩ ።“ብዙ ሰው ችግርን ቢያየውም ሲያልፍለት ይረሳዋል ከረሳው ደግሞ እንደኔ እምነት አላየውም ባይ ነኝ” አለች ኮስተር እንዳለች።

“ጥሩ ፈላስፋ ሳትሆኝ አትቀሪም” አልኳት ከዚያ አይነት ስሜት እንድትወጣ ለማድረግ እንደ መሳቅ ብዬ። “እንዴት ማለት?” አለች እሷም ፈገግ እያለች ጥርሶቿን ሳያቸው በጣም ያማምራሉ። “ነገሮችን ማክበድ ትወጃለሽ” አልኋት ድንጋጤዬን ለመደበቅ እየሞከርኩ። ምጥንን በፊትም አውቃታለሁ ዛሬ ግን ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ በጣም አምሮባታል። ጥርሶቿ ብቻ ሳይሆን ዓይኖቿም የሚስቁ ይመስላሉ ። የለበሰችው አጠር ያለች ጉርድ እና ሰማያዊ ቲሸርት ሲሆን ከወገቧ በላይ ትንሽዬ ነጠላ አጣፍታለች። ባቶቿን አይኋቸው እጅግ ውቦች ናቸው።ማስተዋል ጎድሎኝ ይሁን እንጃ ብቻ እንደዛሬው አምሮባት አይቻት አላውቅም።

ታች ቤት እስከምንደርስ ብዙ ቁም ነገሮችን አጫወተችኝ። አስተማሪወቿንና የታችቤት ነዋሪዎችን በማስተባበርና ብር በማሰባሰብ ለብዙ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት የጥርስ መፋቂያ ሽጠው ህይወታቸውን እንዲቀይሩ ያደረገች ሲሆን አንዳንዶቹ ግን የሰጠቻቸውን ገንዘብ በማጥፋት ወደ ቅፈላቸው እየተመለሱ እንዳስቸገሯት ስትንገረኝ በልቤ “ምስኪን የኔ እናት ምን አለበት እንደ አንቺ ዓይነት ሰዎች መንታ መንታ ቢወለዱ” ከማለት ውጪ ለአድናቆቴ መግለጫ ቃላት ነጥፈውብኛልና  አንዲት ቃል ትንፍሽ አላልኩም።

“በምግባር ያደገች የጌታ ልጅ ጌታ፣
መስጠት የለመደች ማርዳዋን ሳትፈታ፤” ማለት ለእርሷ ነው  እንግዲህ

No comments:

Post a Comment